የእሥራኤልን ሦስት የፓርላማ አባላት ያካተተው የጤና ባለሙያዎች ቡድን፤ ሀገራችን ውስጥ በተከሰተው የጦርነት አደጋ መንስዔ በተጎዱ የጤና ተቋማት የሚያካሂደውን ይፋዊ ጉብኝት በዛሬው ዕለት ጀመረ፡፡

በአጠቃላይ 13 አባላትን የያዘው ይኸው የእሥራኤል ቡድን በኢትዮጵያ በሚኖረው የሦስት ቀናት ቆይታው፤ ለጦርነት ተጋላጭ ሆነው በቆዩት ክልሎች ውስጥ የሚገኙትን የተጎዱ የጤና ተቋማት እንደሚጎበኙ የቡድኑ መሪ ሚስተር ጋዲ ባርከን አስታውቀዋል፡፡

የቡድኑ መሪ ይህንን ያስታወቁት የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፤ የልዑካን ቡድኑን ዛሬ ጠዋት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦሌ ዓለም-አቀፍ ማረፊያ ተገኝተው በተቀበሉበት ወቅት በሰጡት መግለጫ ነው፡፡

የእሥራኤል የፓርላማ አባል እና የቀድሞው የሀገሪቱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ምክትል ሚኒስትር የነበሩት ሚስተር ጋዲ ባርከን በዚሁ ወቅት፤ የልዑካን ቡድኑ የአሁኑ ጉብኝት፣ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቶ ድጋፍ ለማድረግ እና እሥራኤል በችግር ጊዜም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ለማሳየት የታለመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ባርከን አክለውም፤ የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት በጦርነቱ የተጎዳው ሕዝብ ሕክምና እንዲያገኝ የሚረዳ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ዶ/ር ዲማ በበኩላቸው፤ የልዑካን ቡድኑ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ጎብኝቶ ድጋፍ ለማድረግ በመምጣቱ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ሰብሳቢው አያይዘውም፤ ቡድኑ በሦስት ቀናት ቆይታው ከጉብኝት በተጨማሪ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ለወደሙ የጤና ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ለመወያየት መዘጋጀቱንም በአድናቆት ተመልክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባል የተከበሩ አቶ ባያብል ሙላትም በበኩላቸው፤ በእሥራኤል የፓርላማ አባል በተበከበሩ ሚስተር ጋዲ ባርከን አነሳሽነት የልዑካን ቡድኑ መምጣቱ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አቶ ባያብል አክለውም፤ ሌሎች የጤና ባለሙያዎችም ከዚህ በፊት መምጣታቸው እና አሁንም ተመሳሳይ ጉብኝት መደረጉ ሀገራችን ከእሥራኤል ጋር ያላትን የረጅም ጊዜ መልካም ግንኙነት እንደሚያመላክት አስረድተዋል፡፡