የገቢ ግብርን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ ለቋሚ ኮሚቴው ተመራ

 (ዜና ፓርላማ) ሰኔ 27፣ 2017 ዓ.ም፤ ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በዝርዝር ለሚመለከተው የፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በምክር ቤቱ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚንስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ አጭር ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በገቢ ግብር አዋጅ ላይ የተደረገው ማሻሻያ የኢትዮጵያን የግብር ስርአት ዘመናዊ በማድረግ የታክስ ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ፣ የታክስ ህጎች እንዲከበሩ ለማድረግና የመንግስትን ገቢ ለማሳደግ የአዋጁ መሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ባቀረቡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

ረቂቅ የገቢ ግብር ማሻሻያ አዋጁ ዋነኛ አላማዎች ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ያለውን የግብር ጫና መቀነስ፣ የግብር መሰረትን ማስፋት፣ ለአነስተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች ቀላል የግብር አከፋፈል ስርዓት መዘርጋት፣ ለኢንቨስትመንት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ የታክስ ማጭበርበር ጥረቶችን ለመከላከል እንዲሁም ግልጽነት በሚጎድላቸው አንቀጾች ምክንያት የሚደርሱ ውጣ ውረዶችን ማስቀረት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡   

የአገራችንን ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ የግብር ስርአቱን ከአለማችን ልምድ ጋር ማጣጣም የሚያስችል የማሻሻያ አዋጅ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

በተለይም በዲጂታል ዘመን በታክስ አሰባሰብ ረገድ ሊኖር የሚችለውን ፈተና ከግምት ውስጥ በማስገባት የታክስ መሰረትን ማስፋትን እና ፍትሃዊነትን ማረጋገጥን የመሳሰሉ መንታ ግቦችን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ረቂቅ አዋጁ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ በጥልቀት ሊያየው ይገባል ያሏቸውን ሀሳቦች አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 25/2017 አድርጎ ለዝርዝር እይታ ለፕላን በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።