የፓርላሜንታሪ ጥናትና ምርምር ለፓርላማው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለፀ
የፓርላሜንታሪ ጥናትና ምርምር ለፓርላማው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ተገለፀ
(ዜና ፓርላማ) ሐምሌ 3 ፣ 2017 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ ፤ የፓርላሜንታሪ ጥናትና ምርምር ለፓርላማው ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የሙያዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ኃላፊ ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር) ይህን ያሉት በ5ኛው የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ላይ በሀገር ደረጃ 5 ዓመታትን ያስቆጠረውን የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ ሂደትን በተመለከተ ባቀረቡት ወቅት ነው።
በዚህም መሰረት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በህገ-መንግስቱ የተሰጠውን ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት በጥናትና ምርምር ሊደግፉ ከሚችሉ ከፍተኛ የትምህርት እና የምርምር ተቋማት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ የሙያ ማህበራት ከተውጣጡ ተቋማት ጋር “የፓርላማ ጥናትና ምርምር ቅንጅት ወይም የግንኙነት ስርዓት” ዘርግቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም የመጀመሪያው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ የካቲት 12 እና 13 /2013 ዓ.ም. “ፓርላማ ፣ ዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብት” በሚል የትኩረት መስክ 15 የጥናትና ምርምር ስራዎች ቀርበው ከፍተኛ ውይይት እንደተደረገባቸው አንስተዋል፡፡
ይህ እንደ ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ መሰረት የጣለ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሁለተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ ሰኔ 16 እና 17 /2014ዓ.ም. “ፓርላማ ፣ በዲሞክራሲያዊ ሽግግር” በሚል የትኩረት መስክ 14 የጥናትና ምርምር ስራዎች መቅረባቸውን ጠቁመዋል።
ሶስተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ ደግሞ ሰኔ 24 እና 25 /2015ዓ.ም. “ሕግ አወጣጥ ፣ የፓርላማ ክትትል እና ቁጥጥር እና የሕዝብ ውክልና” በሚሉ የትኩረት መስኮች 13 የጥናትና ምርምር ስራዎች ውይይት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ አራተኛው ዓመታዊ የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፍረንስ ሐምሌ 1 እና 2 /2016ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፓርላማ የሀገሪቱ ጥቅም እንዲጠበቅ፤ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም በዲጂታል ዘመን የሀገረ-መንግስት ግንባታ ሒደት ያለው ሚና” በሚሉ የትኩረት መስኮች 11 የጥናትና ምርምር ስራዎች ውይይት መደረጉን አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም ባለፉት 4 ዓመታት በተከናወኑ ፓርላሜንታሪ የጥናትና ምርምር ግኝቶችና ምክረ ሀሳቦችን መሰረት በማድረግ የተተገበሩ አፈፃፀሞች ምክር ቤቱ ህግ የማውጣት ፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራ ፣ የፓርላማ ዲፕሎማሲ አፈጻጸም እና የሕዝብ ውክልና ስራውን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።
ለአብነት ያህልም ባለፉት አመታት የጥናት ውጤቶችን መሰረት ያደረጉ የህግ አወጣጥ ፣ የክትትልና ቁጥጥር ፣ ማንዋሎች ተጠናቀው በምክር ቤቱ እንደ አንድ ወሳኝ የስራ መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
እንዲሁም በውስጥ አቅምና በአጭር ጊዜ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶችን ከማቅረብ አኳያ ያሉ ውስንነቶችን ከመቅረፍ እንዲሁም በርካታ ርዕሰ-ጉዳዮችንም በአንድ ጊዜ ከመዳሰስ ረገድ የጥናትና ምርምር ኮንፍረንሱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
በመጨረሻም "ፓርላማዊ ተግባራትን ማጠናከር ለአካታች አስተዳደር ፣ ለሀገር በቀል ዕውቀትና ለዘላቂ ልማት ! " በሚል መሪ ቃል እየተከናወነ በሚገኘው 5ኛው የፓርላማ ጥናትና ምርምር ኮንፈረንስ እየቀረቡ ያሉ የፓርላሜንታሪ ጥናትና ምርምሮች በምክር ቤቱ አሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ በሚያመጣ መንገድ የሚተገበሩበት ሂደት እንደሚረጋገጥ አብራርተዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives