ዜና ፓርላማ) ህዳር 14/2016ዓ.ም ፤ አዲስ አበባ፤ የፓን አፍሪካ ፓርላማ ይበልጥ እንዲጠናከር ሁሉም አባል ሀገራት በመቀራረብና በመተባበር መስራት እንደሚገባቸው ተጠባባቂ ፕሬዘዳንቱ የተከበሩ ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ አሳሰቡ።

ላለፉት አምስት ቀናት በአዲስ አበባ፣ ቡጁምቡራ እና ሚድራንድ ከተሞች የተካሄደው የፓን አፍሪካ ፓርላማ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች የጋራ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ አፍሪካዊያን በጋራ ችግሮቻቸው ላይ የሚመክሩበትና የመፍትሄ ሀሳብ የሚያመነጩበት እንደመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በመቀራረብና በመተባበር መስራት እንደሚገባቸው የተከበሩ ዶ/ር አሸብር ባቀረቡት የመዝግያ ንግግር ተናግረዋል።

የጋራ ስብሰባው ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ህጋዊ ያልሆነ የመንግስት ምስረታ፣ የፓርላማ ዲፕሎማሲ እንዲሁም በተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ነበር።

ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስትን ጨምሮ ህጋዊ ያልሆነ የመንግስት ምስረታ ለአፍሪካ ሀገራት የዲሞክራሲ፣ የሰላም፣ የጸጥታ እና የዕድገት ጠንቅ ሆኖ መቆየቱን በተደረገው ውይይት የተገለፀ ሲሆን፤ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግሮችን ለማበረታታት፣ ህገ-መንግስታዊነትን ለማስፈን እና ዴሞክራሲን በአፍሪካ አህጉር ለማስፋፋት የሚያግዙ ምክር ሀሳቦች ቀርበዋል።

በአፍሪካ ህገ- ወጥ የሰዎች ዝውውር እየተባባሰ መምጣቱን የሚያስረዱ ጥናታዊ ፅሁፎች በጉባዔው ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን፤ ቀደም ባሉት ጊዚያት የፓን አፍሪካ ፓርላማ ችግሩን ለመቅረፍ ያስቀመጣቸው ምክር ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑም አቅጣጫ ተቀምጧል።

የፓን አፍሪካ ፓርላማ በአህጉራዊና አለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አጋሮች ጋር በመሳተፍ በፖርላማ ዲፕሎማሲው ስራ ወሳኝ ሚና እንዲኖረውም በጉባኤው ከቀረቡ ምክር ሀሳቦች አንዱ ነው።

በመጨረሻም ተጠባባቂ ፕሬዚዳንቱ ላለፉት አምስት ቀናት በተካሄደው የጋራ ስብሰባ ላይ በመገኘት ለተሳተፉት የፖን አፍሪካ ፓርላማ አባላት እንዲሁም ለጉባኤው ስኬት አስተዋጽኦ ላደረጉት የኢትዮጵያ፣ የደቡብ አፍሪካ እና የቡሩንዲ መንግስታት ምስጋና አቅርበዋል።

(በ አበባው ዮሴፍ)

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR

በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ።