(ዜና ፓርላማ)፤ ግንቦት 29፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በድርቅ እና በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች ተገቢውን የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት በማመቻቸት፣ በፍጥነት እንዲያገግሙ ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸው አሳሰበ፡፡

ምክር ቤቱ ማሳሰቢያውን የሰጠው፤ ዛሬ ባካሄደው 5ኛው ልዩ ስብሰባ የግብርና ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ9 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት ነው፡፡

በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ ምክንያቶች ለድርቅ አደጋ እንዲሁም ግጭት በተፈጠረባቸው ስፍራዎች የነበሩት እና አሁንም እዚያው አካባቢ የሚኖሩት ዜጎች፤ ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲያገግሙ ተገቢው የማዳበሪያ እና የምርጥ ዘር አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው፤ ምክር ቤቱ አመልክቷል፡፡

የሪፖርቱን አፈጻጸም አስመልክቶ ከግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከምክር ቤቱ አባላት፤ በርካታ ጥያቄዎች ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ከቋሚ ኮሚቴው እና ከምከር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም በሀገሪቱ የማዳበሪያ አቅርቦት ዕጥረት ለምን ተከሰተ? በሀገሪቱ የተጀመረው የአረንገጓዴ ልማት አፈጻጸም ምን ይመስላል? የቡና ምርት እና ምርታማነትን ለማሻሻል፣ ማዳበሪያን በሀገር ውስጥ ለማምረት ምን እየተሠራ ነው? በድርቅ እና በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን የመደገፍ ሥራ ምን ይመስላል? በግብርናው ዘርፍ የሥራ ዕድል ፈጠራን ማሳደግ፣ ምርጥ ዘር እና የግብርና ሜካናይዜሽንን ለማዳረስ ምን ታቅዷል? የሚሉት በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ፤ የማዳበሪያ አቅርቦት በሁሉም አካባቢዎች መዳረስ እንዳለበት፣ የአረንጓዴ ልማት ሥራ የዘመቻ ጉዳይ ብቻ መሆን እንደሌለበት እና ጠቀሜታ እና ወጪ በየጊዜው መገምገም እንዳለበት፣ ቡና የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ምንጭ በመሆኑ አሮጌ የቡና ተክል በመጎንደል፤ ምርታማነትን መጨመር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

አያይዘውም፤ ከውጭ በከፍተኛ ምንዛሪ የሚገባውን ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለማምረት የተጀመሩ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር የሚጠናቀቁበትን መንገድ መፈለግ እና ኮምፖስትን በማዘጋጀት እና በመጠቀም የማዳበሪያን ፍላጎት ማርካት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ለአርሶ-አደሩ የተለያዩ የግብርና ሜካናይዜሽኖችን ተደራሽ በማድረግ፤ በዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጠር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በይበልጥ ለመሥራት ማሰቡንም ሚኒስትሩ ለፓርላማው አብራርተዋል፡፡

በ ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ