በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፤ “የሀገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማስከበር፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስርን ማጎልበት ያስፈልጋል” በማለት አቅጣጫ አመላከተ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ይህንን ያመላከተው፤ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ሰሞኑን በገመገመበት ወቅት በሰጠው አቅጣጫ ነው፡፡

በሀገራችን ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ትስስርን በማጎልበት፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የሚነሱ ግጭቶች እንዲፈቱ፤ የመሠረተ-ልማት እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር መፍጠር ለነገ የሚተው ተግባር እንዳልሆነ ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡ በዚህም ረገድ የተጀመሩ የድጋፍ እና የክትትል ሥራዎች እንዲጠናከሩ፤ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በሰጡት ሐሳብ፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ግጭት ዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ በያዘው የተዛባ አመለካከት የተፈጠረውን የዲፕሎማሲ ጫና እና የውጭ ግንኙነት ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍን ከማሳደግ አንጻርም በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ሰብሳቢው አያይዘው አስገንዝበዋል፡፡

የሱዳን መንግስት ዓለም-አቀፍ ሕግን እና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በመጣስ በድንበር አከባቢ ወረራ መፈጸሙን ተከትሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም፤ ከዘላቂ መፍትሔ አኳያ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ፈቲ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በዓለም-አቀፍ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ዙሪያ የተከናወኑ የጥናት እና ምርምር ሥራዎችን ተግባራዊ ከማድረግ፤ የኢኮኖሚ ጫናን ለመፍታት ኢንቨስትመንት በማፈላለጉም ሆነ በዘርፍ አመርቂ ውጤት ያመጡትን በማበረታታት፤ የዜጎችን መብት እና ጥቅም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፤ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የተደረገው ሪፎርም ሀገራዊ ዲፕሎማሲያችንን እና ብሔራዊ ጥቅማችንን ከማስጠበቅ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ነገር ግን ስኬታማ ዲፕሎማሲ እንዲኖር የውስጥ ሰላማችንን ማዳበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሱዳንን ወረራ አስመልክተው በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም፤ አሸናፊነታችንን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ልዩነቶችን እና ችግሮችን በሰላም አማራጮች በመፍታት፣ ዘላቂ ጥቅምን ማስጠበቅ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በሀገሪቱ ሕገ-መንግስት መሠረት ስለሀገሪቱ ሕዝቦች ሰላም፣ ስለየብስ እና አየር ክልሎቿ ደኅንነት የሚመለከተው ትልቁ ብሔራዊ ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡