“የብዝኃነታችንን ኅብር ተቀብለን፤ ሀገራችንን ማጽናት አለብን” ሲሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ተናገሩ።

“ኢትዮጵያ እያሸነፈች ትሻገራለች” በሚል መልዕክት የፓናል ውይይት ከሚካሄድባቸው 11 ከተሞች አንዷ በሆነችው ጅግጅጋ ዛሬ የተጀመረውን መድረክ በይፋ የከፈቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ እንደተናገሩት፤ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ሕዝቡን በሀገራዊ ጉዳዮች የሚያወያዩ መድረኮች በዋና ከተሞች ተዘጋጅተዋል።

“ኢትዮጵያ በማሸነፍ እንደምትቀጥል ለማሳየት የሚያስችሉ እና የሕዝቡን አብሮ የመምከር ባሕሉን የሚያጎለብቱ ሕዝባዊ ውይይቶች በቀጣይነት ይካሄዳሉ” አፈ-ጉባዔው እንዳሉት።

አፈ-ጉባዔው አያይዘው እንደገለጹት፤ ረጅም ታሪክ ያለን ሀገር እና ሕዝብ መሆናችንን ለዓለም ለማሳየት፣ ስለ ኢትዮጵያ ያገባኛል የሚሉ አካላት በእነዚህ መድረኮች ተገኝተው ሀገራችንን የሚጠቅሙ ሐሳቦች እንዲያካፍሉ ጥሪ ቀርቧል።

የሶማሌ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሐመድ በበኩላቸው፤ በሀገራዊ ጉዳይ የተዘጋጀው መድረክ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፣ ታዳሚዎች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በፓናል ውይይቱም፤ በምሁራን የተዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

በመድረኩም፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት፣ የሲቪክ ድርጅቶች ተወካዮች እና አርቲስቶች እንዲሁም ጋራድ ኩልሚዬ ገራድ መሀመድ፣ ኦጋዞች፣ ሱልጣኖች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በሌላ በኩልም፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ”ስለ ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ያዘጋጀው የፎቶግራፍ ዐውደ-ርዕይ፣ እስከ መጪው ሐሙስ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ፤ ኢዜአ ከስፍራው ካሠራጨው ዘገባ መረዳት ተችሏል።