"ምክር ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ ስምምነቶችን በማፅደቅ እየሰራ ይገኛል" - የተከበሩ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር)
"ምክር ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ ስምምነቶችን በማፅደቅ እየሰራ ይገኛል" - የተከበሩ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር)
----------------------
(ዜና ፓርላማ)፣ ሚያዚያ 16፣ 2016 ዓ.ም.፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተለያዩ ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ ስምምነቶችን በማፅደቅ እየሰራ ይገኛል ሲሉ የጤና፣ማሕበራዊ፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ይህ የተገለጸው የምክር ቤቱ የጤና፣ ማሕበራዊ፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሴቶች ማሕበራዊ እንቅስቃሴ፣ በፓለቲካዊ ተሳትፎ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም በምክር ቤቱ ስልጣንና ተግባራት ዙሪያ ከደቡብ ሱዳን ከመጡ የተለያዩ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ውይይት ባካሄደበት ወቅት ነው።
የውይይት መድረኩን የመሩት የጤና፣ማሕበራዊ፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተለያዩ አለማቀፋዊና አህጉራዊ ስምምነቶችን ተቀብላ በማፅደቅ እየሰራች እንደሆነ ገልፀው፥ የፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥ፣ ፆታዊ ጥቃትን ከመከላከል እንዲሁም የሴቶችን የኢኮኖሚ አቅም ከማጎልበት አንፃር የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ገልጸዋል።
የፓርላማ ተመራጭ ሴቶች ኮከሱ ሰብሳቢ የተከበሩ ኪሚያ ጁንዲ ፤ በተለያዩ ጊዜያት ለሴቶች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት አቅማቸው ተገንብቶ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ህግ የማውጣት፣ የቁጥጥርና ክትትል፤ የህዝብ ውክልና ሥራ እንዲሁም የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሰሩ ለማስቻልና በሁሉም ዘርፎች የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ለቡድኑ ገልጸዋል።
የሴቶችን ብቃትና አቅም በማጠናከር በርካታ ለውጦች መገኘታቸውንና ተጨባጭ ለውጥ አሳይተዋል፤ ተሞክሮውም በጎረቤት ሀገራት እንዲተገበር ፍላጎት አለን ሲሉ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል።
የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ፈቲ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በትምህርቱ ዘርፍ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርትና ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እየተማሩ እንደሚገኙ ገልጸው፤ በቀጣይም ይህንን ግንኙነት በማሳደግ በሁለቱ ሀገራት መካከል የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የንግድ ልውውጥ ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ሱዳን ፕሬስ ሴክሬታሪ ዳይሬክተር ኤስቴር ፊክሬ በበኩላቸው ሴቶች በፖለቲካና ኢኮኖሚ ተሳታፊ እንዲሆኑ በአመራር ሰጪነት እንዲሳተፉ ኢትዮጵያ የተገበረችው ለደቡብ ሱዳን በተሞክሮነት የሚወሰድ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በመድረኩም ከደቡብ ሱዳን የመጡት የተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በኮከሱ እና በፓርላማው ስልጣንና ተግባራት ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየት ያነሱ ሲሆን በኮከሱ አባላትና በሚመለከታቸው የምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
(በሚፍታህ ኪያር)
ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/@FDREHOPR
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives