(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 7፣ 2014 ዓ.ም.፤ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “በኢትዮጵያ በተካሄደው ሁሉን-አቀፍ ሀገራዊ ለውጥ አስደማሚ ውጤቶች ተመዝግበዋል” ሲሉ የለውጡን ውጤት ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በሪፎርሙ ዐበይት የልማት ግቦችን በተሻለ ብቃት እና አፈጻጸም ማሳካት እንደቻለች የገለጹት፤ ዛሬ በተካሄደው 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 13ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የምክር ቤቱ አባላት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ እና ክስተቶችን አስመልክቶ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ በልማት፣ በመልካም አስተዳደር እና በማኅበራዊ ዘርፎች ያተኮሩ ነበሩ፡፡

“የኢትዮጵያን ዕድገት እና ብልጽግና በዘላቂነት ለማረጋገጥ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ እና ለልማት ፕሮጄክቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ቢሆንም፤ በምርቶች ላይ የዋጋ ግሽበት የሚስተዋል በመሆኑ፣ መንግስት ለምን አፋጣኝ መፍትሔ አይሰጥም?” ሲሉ የምክር ቤት አባላት ጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት፤ “የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የኢትየጵያውያንን አብሮ የመኖር ዕሴት የሚንዱ ጽንፈኝነትን እና ዘረኝነትን ለማሰቀረት መንግስት ምን ርምጃ እየወሰደ ነው?” ሲሉም ጥያቄያቸውን አክለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ሁለንተናዊ ጥረት እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም፤ ስንዴ ለማኟ አፍሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ አስደማሚ ታሪክ በመሥራት፣ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ስንዴ ለዓለም ገብያ እንደምታቀርብ አስታውቀዋል፡፡

ምንም እንኳን የባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ በችግሮች የታጀበ ቢሆንም፤ በግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ እና በልማት ፕሮጄክቶች ተጨባጭ ውጤት ማምጣት እንደተቻለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

“በመንገድ ዝርጋታ፣ በቴሌ-ኮሚዩኒኬሽን ሽፋን እንዲሁም በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሌሎች የሀገሪ ቁልፍ ተቋማት፤ ሀገራዊ ሪፎርሙ እመርታዊ ለውጥ በማምጣት፤ ለማመን የሚከብድ አስደማሚ ውጤት ማምጣት ችለናል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አብራርተዋል፡፡

የዜጎችን ሰላም እና ደኅንነት በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምለሽ ሲሰጡ፤ “ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት፤ አብሮነት እና የዜጎችን ሰለም የሚያደፈርሱ ከውስጥም ይሆን ከውጭ ሚቃታብንን ትንኮሳ ለድርድር አናቀርበውም፡፡ ዘላቂ እና የተረጋጋ ሀገር ለመፍጠር ምንጊዜም እንተጋለን” የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሌብነትን እና ብልሹ አሠራሮችን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዋናነትም ፍርድ ቤቶች፣ ዐቃቤ-ሕግ፣ ፖሊስ እና ኦዲተር በዚህ አስጸያፊ ተግባር የተዘፈቁ መሆናቸው በጥናት የተረጋገጠ በመሆኑ፤ ርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል፡፡

የኃይማኖት ተቋማትም የሌብነት ሰለባ በመሆናቸው በቀጣይ ኦዲት እንደሚደረጉ እና በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት የአሠራር ሥርዓት የሚዘረጋ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን እና የዋጋ ንረትን መግታት የምንችለው ቆርጠን ወደ ልማት በመግባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያን ዕድገት እና ብልጽግና ዕውን ማድረግ የሚቻለው፤ ስንፍና-አዘል ስግብግብነትን እና የሞራል ዝቅጠትን ማስቀረት ስንችል ነውም ብለዋል፡፡

በተመሳሳይም የውጭ ሀገራትን አሉታዊ ተጽዕኖ መገዳደር፣ ትውልድ ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት እንዲሁም ሥራ-ጠልነትን በሚገባ መጋፈጥ ከቻልን፤ የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልጽግና ማረጋገጥ የሚቻል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ