“በሪፖርቱ ብዙ የተሻሻሉ አፈጻፀሞች ታይተዋል -- ቋሚ ኮሚቴው”
“በሪፖርቱ ብዙ የተሻሻሉ አፈጻፀሞች ታይተዋል -- ቋሚ ኮሚቴው”
በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከዚህ ቀደም በድክመት ከተነሱ አፈፃጸሞች አንፃር የተሻሻሉ ሆነው ቀርበዋል ሲሉ ገልፀዋል።
የልማት ፕሮጀክቶችን በሚመለከት ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቶች በዝርዝር ይዘጋጅ ብሎ ከዚህ ቀደም ብሎ በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በዚህ ሪፖርት መካተቱ በጥንካሬ የሚነሳ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል የልማት እቅድና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ውጤታማነትን የማሻሻል ግብ ላይ በተለይ የልማት ኘሮጀክት ቅድመ አዋጭነት ጥናት ጥሩ ጅምር ቢታይበትም አሁንም ሀብት ፈሶ ጥቅም ላይ በአግባብ የማይውል ከሆነ የመልካም አስተዳደር ችግርና የቅሬታ ምንጭ ሊሆን ይችላል ሲሉ ገልፀዋል።
ስለሆነም ነባር፣ እየተሰሩ ያሉትንም ሆነ ያለቁ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እየተመዘኑ እየተመጠኑ አዋጭነታቸው ብቻ ሳይሆን ፍትሀዊነታቸውም እየታየ መሰራቱን ማረጋገጥ የሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ትልቅ ኃላፊነት መሆኑን ከግምት በማስገባት መስራት እንደሚገባም ነው የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ያሳሰቡት።
አያይዘውም የክልሎች ዕቅድና የዘርፍ እቅድን በሚመለከት ሁለቱንም እናስተሳስራለን የሚለው ሀሳብ በየአመቱ ሪፖርት ላይ ይቀርባል ነገር ግን ተግባራዊ እየሆነ አይደለም ብለዋል።
ከክልሎች ጋር እቅዱን የማናበብና አፈፃፀሙን በየሩብ ዓመቱ የመገምገም ስራ እቅድ ላይ በተቀምጠው መሰረት ወደ ተግባር ለመቀየር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የተከበሩ አቶ ደሳለኝ የአካባቢ ጥበቃ እና ቁጥጥርን ከማሻሻል አኳያ ትልቅ ስራ የተጀመረ መሆኑን፣ የአካባቢ ጥበቃ ህጎች የበለጠ ተጠናክረው እንዲሄዱ ብዙ የተደራጁ ስራዎች ተሰርቷል ነገር ግን ቀጣይነት እንዲኖረው ህግና አሰራሮችን ጠብቆ በተቋም ደረጃ ሊሰራ ይገባልም ሲሉም አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም ሰብሳቢው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ያነሳቸውን ሀሳቦች በቀጣይነት ይዞ መሄድ፣ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አብርሀም አለማየሁ (ዶ/ር) የመንግስትን የፕሮጀክት አፈፃፀምና ኢንቨስትመንትን ለመከታተል እና ለማሻሻል ከፕሮጀክቶች አዋጪነት ጥናት ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ ያሉ አፈፃጸሞች በጥንካሬ የሚነሱ ናቸው ብለዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives