"በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል"
"በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል"
----- አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ -----
(ዜና ፓርላማ) ሚያዝያ 17፣ 2017 ዓ.ም፤ በኢትዮጵያ እና በግሪክ መካከል ያለው የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ገልጸዋል፡፡
በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ዶ/ር ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ የተመራው የልኡካን ቡድን በዛሬው እለት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
የልኡካን ቡድኑ ከተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ እና በምክር ቤቱ የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተዋል፡፡
የተከበሩ አፈ ጉባኤ በዚሁ ወቅት ሲናገሩ ሁለቱ አገራት ለበርካታ ዓመታት ያዳበሩት ጠንካራ የመንግስታት እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከግሪክ ንግድና ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች ልምድ መቅሰም እንደምትፈልግና ያላትን መልካም ተሞክሮም ለማካፈል ያላትን ዝግጁነት የተከበሩ አፈ ጉባኤ ለልኡካን ቡድኑ አስረድተዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ እና የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት የወዳጅነት ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና ግሪክ ለረጅም አመታት ያላቸውን ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በሃይል / ኢነርጂ እና በተለያዩ ዘርፎች ተባብረው ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የተከበሩ አምባሳደር ዲና አመላክተዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ምክር ቤቶች ተቀራርበው በመስራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በግሪክ ፓርላማ አባልና የኦርቶዶክስ ኢንተርፓርሊያመንት ጉባኤ (IAO) ኃላፊ ዶ/ር ማክስሞስ ቻራኮፖሎስ በበኩላቸው ግሪክ የአውሮፓ ህብረት አባል እንደመሆኗ ኢትዮጵያን ከአውሮፓ ህብረት ጋር ለማቀራረብ እንደምትሰራ ገልጸዋል፡፡
በቱሪዝም እና በግብርናው ዘርፍ ግሪክ ከኢትዮጵያ በርካታ ልምዶችን መቅሰም ስለምትፈልግ በዘርፉ አብሮ ለመስራት ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎትም ጠቁመዋል፡፡
ግሪክ በኮንስትራክሽን፣ በባህር ትራንስፖርት እና በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል እንደምትፈልግና የግሪክ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቬስትመንት ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባ ዶ/ር ማክስሞስ አስረድተዋል፡፡
(በ አበባው ዮሴፍ)
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives