"በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
"በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 26 ቀን ፣ 2017 ዓ.ም፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው በ42ኛ መደበኛ ስብሰባው ተገኝተው የመንግስትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል የሀገሪቱን ሰላምና ጸጥታ የሚመለከቱ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ተነስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠቁመዋል።
የስንፍና ፖለቲካ በሀገራችን መንሰራፋት፣ በኃይል የታገዘ ፖለቲካ ማራመድ፣ ድህነትና ስራ አጥነት እንዲሁም ኋላቀርነት እና ዘረኝነት በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ጸጥታ እንዳይፈጠር አባባሽ ችግሮች ስለመሆናቸው አስረድተዋል፡፡
የስንፍና ፖለቲካ ግጭት፣ ፀብ፣ ተቃርኖን ይወልዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአሁኖቹን ፖለቲከኞች እንደ ድሮ ዘመን መሳፍንቶች እና መኳንንቶች “ሳትሠራ አትብላ” የሚለውን መርህ እንደማይቀበሉና ገበሬው ያረሰውን እንደሚካፈሉት መኳንንቶች ናቸው ሲሉም ገልጸዋቸዋል።
አውርቶ አደር ፖለቲከኞች ዋና ሥራቸው አባልተው መብላት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ካላጋጩ እና ካላባሉ ስለማይበሉ ግጭት በመፍጠር ጎፈንድ ሚ ወይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ደመወዝ ይሰበስባሉ ብለዋል።
እነዚህ እሳቤዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ታክሎበት የባንዳነት ስሪት ደግሞ በመስፋቱ ችግሩን አባብሶታል፤ ኢትዮጵያ ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች አሉ፤ ኢትዮጵያውያንም እሳት ጫሪዎችን ማወቅና ማረም ያስፈልጋል” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ክላሽ ካነገትኩ ፍላጎቴ ይሳካል ብለው የሚያምኑ በህዝብ የተመረጠን መንግስት በኃይልና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያምኑ ቡድኖች ፍላጎት እንደማይሳካም ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ሀይሎች ሀይልን በበላይነት መጠቀም የሚችለው መንግስት መሆኑን የማይቀበሉ እንደሆኑ አስረድተው፤ የፖለቲካ ሀሳብን በምርጫ እንጂ በጠመንጃ ማሳካት አይቻልም ብለዋል።
በትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ሀይሎች የሰላም አማራጭን ቀዳሚ ሊያደርጉ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
እነዚህን ሀይሎች ማህበረሰቡ በቃችሁ ሊላቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ በተለያዩ ጊዜያት ህዝቡ የአጥፊ ሀይሎች እኩይ ተግባር በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ መውጣቱን አስታወሰዋል፡፡
መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ለአፍራሽ ሀይሎች ምቹ እድልን የሚፈጥረውን ድህነት እና ኋላቀርነት ለመቅረፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ማህበረሰቡ ሳይሸሽግ የታጠቁ አካላትን አትግደሉ፣ አትግደሉልኝ፣ እናንተም አትሙቱልኝ ማለት አለበት ሲሉ ገልጸው፤ ልጆቼን ፈተና እንዳይፈተኑ እንዳይማሩ አትከልክሉ፣ እንዳንሰራ አታድርጉ፣ ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ ማለት እንደሚገባው ጠቅላይ ሚንስትሩ አሳስበዋል፡፡
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives