(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 02፣ 2014 ዓ.ም.፤ አዲስ አበባ፤ በኮንስትራክሽን እና በመሠረተ-ልማት ግንባታ ዘርፎች የኢትዮጵያ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የከተማ፣ መሠረተ-ልማት እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ገለጹ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ይህን የገለጹት፤ በዛሬው ዕለት ፓርላማው በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12ኛ መደበኛ ስብሰባው፣ የከተማ እና መሠረተ-ልማት ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት የ10 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ሕዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት፤ በሀገሪቱ የተጀመረው ሁሉን-አቀፍ  ሪፎርም ዕውን መሆኑን ለማረጋገጥ እንዲቻል፣ ከተሞችን የብልጽግና ማዕከል ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆኑን  የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ  ክብርት ሸዊት ሻንካ አስገንዝበዋል፡፡ ከቤቶች ግንባታ አፈጻጸም እና አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የ2014 በጀት ዓመት ከዕቅዱ አንጻር ሲገመገም፤ የሥራ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንደሆነ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት የተጀመሩ የሕንፃ ፕሮጄክቶች ብዙ ገንዘብ ወጪ ከተደረገባቸው በኋላ ግንበታቸው እየተቋረጠ መሆኑን ሰብሳቢዋ ጠቁመው፤ በሌላ በኩል መንግሥት በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት የቢሮ ሕንጻ መከራየቱ አላስፈላጊ የሀብት ብክነት ስለሆነ፤ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈለግለት አሳስበዋል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በከተሞች የሚስተዋሉ ውስብስብ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በክላስተር ከፋፍሎ ድጋፍ ማድረጉ፣ በምግብ ዋስትና  እና በከተሞች የውስጥ ገቢ አሰባሰብ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገቡ፤ በጥሩ ጎን የሚታይ መሆኑን የተከበሩ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ ገልጸዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ የመንገድ መሠረተ-ልማት ዝርጋታ ለአንድ ሀገር ክፍለ-ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነ ገልጸው፤ የሚገነቡ የመንገድ ፕሮጄክቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ እንዳለባቸው አመላክተዋል። ከሚያስገኙት ፋይዳ እና  ከፍትሐዊ ተደራሽነት አንጻርም ዘርፉ በትኩረት መታየት እንዳለበት አንስተዋል፡፡

በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንገድ እጦት፣ የተደራሽነት እና የብልሽት ችግር እንዳለ እና የሕዝቡ የመልማት ጥያቄ አንገብጋቢ እና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን የምክር ቤት አባላት አመልክተዋል፡፡

ፕሮጄክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባሕል ሊኖር ይገባል ያሉት የምክር ቤት አባላት፤ ፕሮጄክቶች ግንባታቸው  በተጓተተ ቁጥር በሕዝቡ እንደ መልካም አስተዳደር ችግር እየታዩ በመምጣታቸው፣ የችግሮች ስፋት በጥልቀት ታይቶ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጥበት ይገባል ብለዋል፡፡

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ