“የምክር ቤቱን ተግባራት በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል”
“የምክር ቤቱን ተግባራት በቴክኖሎጂ በመደገፍ ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ ለማስቻል ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል”
---- የተከበሩ አፈ-ጉባዔ ታገሠ ጫፎ -----
(ዜና ፓርላማ) ግንቦት 4 ፣ 2017 ዓ.ም፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያከናውናቸውን የተለያዩ ተግባራትና የአሰራር ስርዓቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ በማስቻል ሕብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ ቅድሚያ ተሰጥቶ ይሰራል ሲሉ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ታገሠ ጫፎ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ ክንውን በምክር ቤቱ የአማካሪ እና አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በጋራ ተገምግሟል።
በዚሁ ጊዜ ምክር ቤቱ ህጎችን የሚያወጣበት ዋና አላማ በህብረተሰቡ ዘንድ ለሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከመሆኑ አንጻር ሕጎችን ከማርቀቅ አስከ ማፅደቅ ባለው ሂደት ማህበረሰቡ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻል እንደሚገባ የተከበሩ አቶ ታገሰ አስገንዝበዋል፡፡
ይህንንም ከግብ ለማድረስ የምክር ቤቱን የአሰራር ስርዓት ጊዜውን በዋጁ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በማስደገፍ ህብረተሰቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
የምክር ቤቱ ምክትል አፈ-ጉባዔ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ በሚያከናውናቸው የክትትል እና ቁጥጥር ስራዎች ወቅት ሕብረተሰቡ የተለያዩ ጥያቄዎችን እንደሚያነሳ ተናግረው፥ ምክር ቤቱ ለጥያቄዎቹ ተገቢውን ምላሽ በማይሰጡና ሃላፊነታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት እየሰራው በሚገኘው አደረጃጀት ሠራተኞች ብቁና ተወዳዳሪ በሚሆኑበት የሥራ ዘርፍ የሲቪል ሰርቪስ ህግና መመሪያ በሚፈቅደው መሰረት ተወዳድረው ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎች መጠናቀቃቸውንም የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ አስታውቀዋል።
የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚንስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ምክር ቤቱ ባከናወናቸው ሕግ የማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የውክልና እንዲሁም የዲፕሎማሲ ስራዎች የተገኙ ተጨባጭ ለውጦች የሚገመገምበት ስርዓት በመዘርጋት ቀጣይ የሚሰሩ ምክርቤታዊ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም እንዲኖራቸው ለማስቻል የሚያግዙ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶች እንደሚዘጋጁ ጠቁመዋል።
የምክር ቤቱ ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሃፊ (ሙያዊ ዘርፍ) ንጉሤ መሸሻ (ዶ/ር) የምክርቤቱን የ2017 በጀት አመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ ክንውን ሪፖርተር አቅርበዋል፡፡
በምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች አማካኝነት የሕግ ማውጣት፣ የክትትልና ቁጥጥር፣ የሕዝብ ውክልና ሥራዎችን እና የፓርላሜንታዊ ዲፕሎማሲ ተግባራትን በጥሩ ሁኔታ መከናወናቸውን ገልጸው፥ በአጠቃላይ የቋሚ ኮሚቴዎች ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ካቀዱት ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ አፈፃፀም ማሳየቱን በሪፖርቱ ተመላክቷል ፡፡
የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት የዘጠኝ ወሩ አፈጻጸም 86 በመቶ በላይ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይ በስራ ላይ የታዩ ጥንካሬዎችን የበለጠ በማስቀጠልና በማጠናከር ላይ እንደሚያተኩርም ተገልጿል፡፡
በግምገማውም በምክር ቤቱ የአማካሪና የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት የተገኙ ሲሆን ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተሰሩ የተለያዩ ስራዎች የታዩ ጥንካሬዎችና በቀጣይ መስተካከል ይገባቸዋል በሏቸው የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት አድርገዋል።
(በሚፍታህ ኪያር)
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives