(ዜና ፓርላማ)፤ ሰኔ 12፣ 2014 ዓ.ም.፤ ቢሾፍቱ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶ፤ "የፌዴራልም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ፤ በመረጃ እና ማስረጃ መደገፍ አለበት" አሉ።

የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባዔ ይህንን ያሉት፤ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ ሰንብቶ ዛሬ በተጠናቀቀው እና ለክልል ምክር ቤቶች የቋሚ ኮሚቴዎች አመራሮች፣ ለጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ለሕግ ክፍል ዳይሬክተሮች፤ የምክር ቤት ተግባራትን እና ኃላፊነቶችን በተመለከተ በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው በሰጡት የጋራ የሥራ አቅጣጫ ነው።

የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ፤ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ ምክር ቤቶች የሚያካሂዷቸው የክትትል እና ቁጥጥር ተግባራት፣ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ በተሟላ መረጃ እና ማስረጃ መደገፍ አለባቸው ብለዋል። ምክር ቤቶች የተጣለባቸውን ሕገ-መንግስታዊ ኃላፊነት መወጣት እንዲሁም የሕዝብን ጥቅም ማረጋገጥ የሚችሉት፤ በቂ ማስረጃ ሲይዙ እንደሆነም አበክረው አስገንዝበዋል።

"ክትትል እና ቁጥጥር ከተካሄደ በኋላ፤ በተቋሙ ላይ እንደዚሁም ለሕብረተሰቡ ምን ለውጥ መጣ? ምንስ ርምጃ ተወሰደ? የሚሉትን ጉዳዮች ማረጋገጥ ይገባል። ምክር ቤቶች ራሳቸው ርምጃ ባይወስዱም፤ ትክክለኛ መረጃ እና ማስረጃ አቅርበው ሕጋዊ ተጠያቂነት እንዲኖር ያደርጋሉ። በዚህም አካሄድ፤ የሕዝብን እና የሀገርን ጥቅም ያረጋግጣሉ" የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ እንዳብራሩት።

በሌላ በኩል ሕግ ማውጣትን በተመለከተ ሁሉ ነገር ሕግ እንደማይወጣለት የጠቆሙት ምክትል አፈ-ጉባዔዋ፤ ሕጎች መፃዒ ጊዜያትን እና ሁኔታዎችን፤ እንደዚሁም ሀገር የደረሰችበትን አጠቃላይ ምጣኔ-ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊ እና ሌሎችም ሁኔታዎችን ከግንዛቤ አስገብተው እንደሚወጡ አስረድተዋል።

ከክልል ምክር ቤቶች ጋር የሚደረገው መሰል መስተጋብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተከበሩ ወይዘሮ ሎሚ አስታውቀዋል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበኩሉ፤ ዓቅም በፈቀደ መጠን ከክልል ምክር ቤቶች ጋር ተጋግዞ እና ተባብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል።

"የሕግ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት" በሚል ርዕስ የስልጠና ማኑዋል የአቀረቡት ደግሞ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የሕግ አወጣጥ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ አቶ ኤፍሬም ውበት ናቸው። ዳይሬክተሩ በሰጡት ስልጠና፤ ሕግ አውጪው አካል ሕግ በማውጣት ሂደት ሊያያቸው እና ሊመረምራቸው የተገቡ ዐበይት ጉዳዮችን አመልክተዋል።

"በመጀመሪያ ደረጃ ሕጎች ከሕገ-መንግስቱ መቃረን የለባቸውም። ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም-አቀፍ ሕጎች እና ድንጋጌዎች አንጻር የተቃኙ መሆን አለባቸው። ከሌሎች ሕግጋት ጋር ተደጋጋፊ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት። አካል ጉዳተኞችን፣ ሕጻናትን እና አረጋውያንን ማካተት ይጠበቅባቸዋል። የሕግ ድግግሞሽ እንዳይኖርም ጥንቃቄ ያሻል" አቶ ኤፍሬም እንደተናገሩት።

ሌላው እና በደንብ መታየት የሚገባው ጉዳይ፤ ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ ሕግ የማውጣት ስልጣን መኖሩን ማረጋገጥ ነው። ቀጥሎም፤ ሕግ ከማውጣት ውጪ ሌላ አማራጭ አለመኖሩም እንደዚሁ መረጋገጥ አለበት - ርሳቸው እንደአስቀመጡት። ከዚህ ሁሉ ሂደት በኋላ የሚወጣው ሕግ ግን፤ ተፈጻሚ መሆኑን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አቶ ኤፍሬም አመላክተዋል።

በአጠቃላይ የሚወጡት ሕጎች የሕብረተሰቡን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆናቸውን እና ተግባራዊነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ፤ ዳይሬክተሩ በስልጠናቸው አንስተዋል። የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሕጋዊ ቁጥጥርን (Legal auditing) እንዲያግዝ ማኑዋል ማዘጋጀቱን አያይዘው ገልጸዋል።

የሁለት ቀናቱን የስልጠና መድረክ በአወያይነት ከመሩት መካከል፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስተዳደራዊ ዘርፍ ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ ታምር ከበደ ግንባር-ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። ባላቸው የካበተ ምክር ቤታዊ ዕውቀት፣ ግንዛቤ እና ክህሎት ተመርኩዘው፤ ለመድረኩ ተሳታፊዎች ሰፋፊ ማብራሪያዎችን መስጠታቸውን ከስፍራው ሆነን ለመገንዘብ ችለናል።

በ አሥራት አዲሱ