(ዜና ፓርላማ)፤ ሕዳር 6፣ 2015 ዓ.ም፤ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም ክብርት ኘሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ያደረጉትን የመክፈቻ ንግግር አስመልክቶ ከምር ቤቱ ለተነሱ ጥያቄዎች በዛሬው ዕለት ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምር ቤት አባላት ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ዘላቂ ሰላምና ድርድሩን፣ የኢኮኖሚውን እድገትና ተግዳሮቱን፣ እንዲሁም እንደ ሀገር ፈተና የሆኑ የጋራ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲበጅላቸው ፈርጀ-ብዙ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሰላም ድርድሩን በተመከተ ከምክር ቤቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ በሰጡበት ወቅት፤ ሁሌም በጦርነት መኖር እንደማይቻል እና የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማስቀጠል ሲባል ጦርነትን ማቆምና ወደ ሰላም ድርድር መምጣት ፋዳይዳው የጎላ እንደሆነ ታምኖበታል ብለዋል፡፡

በጦርነት ውስጥ ትርፍ የሚያጋብሱ ሀይሎች ሁሌም ሰላም የማይፈልጉ መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በድርድሩ ቃል የተገቡ ጉዳዮች በተግባር እንዲፈጸሙ በትብብር መስራት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱትን አካባቢዎች ለዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ፣ የመሰረተ-ልማት አውታሮችን የመገንባት እና ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን የማህበረሰብ ክፍሎች ደግሞ ወደ የሚኖሩበት ቀዬ የመመለስ ስራው በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የማይቀለበስ እንደሆነ መረጋገጡን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለአብነት በ2014 በጀት ዓመት የግብርናው ክፍለ-ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት ማሳየቱን አስገንዝበዋል፡፡ በ2015 በጀት ዓመት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በ7.5 በመቶ እንደሚያድግ በማስረጃ አስደግፈው ገልጸዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ የታየውን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ማስቀጠል ከተቻለ ኢትዮጵያን የዳቦ ቅርጫት ማድረግ የሚቻል እንደሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስገንዝበዋል፡፡

ኢትዮጵያ የገጠማትን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የማዕድ ማጋራት፣ የተማሪዎች ምገባ፣ በመንግስት የተደገፈ የምርት አቅርቦት ችግሩን ለማስታገስ እንደ መፍትሄ መወሰዱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ መሰረታዊ መፍተሄ በቂ ምርት ማምረት፣ ብክነት መቀነስ፣ ማጋራት፣ መታቀብ እና መምረጥ አይነተኛ ድርሻ ያላቸው መሆኑን በትኩረት አብራርተዋል፡፡

ሥራ አጥነት ለአለም ሀገራት ብሎም ለኢትዮጵያ ፈተና እንደሆነ ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዜጎች የስራ እድል ፈጠራ ረገድ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በትኩረት እየሰራ ስለመሆኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የብሔራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግሮች ከሞላ ጎደል ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የተጣለበት አንደሆነ ገልው፤ ኮሚሽኑ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በመወጣት ውጤታማ እንዲሆን በትብብር መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ሌብነት እንደ በጎ ባህል ተቆጥሮ በሀገር እና በሕዝብ ሀብት ላይ ከፍተኛ ምዝበራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በቅርቡ ኮሚቴ ተዋቅሮ በማጣራት ሌቦችን አንገት የማስደፋት እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን የድጋፍ ሞሽን በ1 ተቃውሞ በ4 ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።

በ ተስፋሁን ዋልተንጉስ

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት 
በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament 
በዩቲዩብ https://www.youtube.com/channel/UCZm9CZOqIyp8qesP3XkVBPg
በቴሌግራም https://t.me/ParlamaNews 
በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr 
በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ