"የ2018 በጀት በከፍተኛ ሁኔታ የገቢ አቅምን ማሳደግ ላይ የተመሰረተ ነው" - ክቡር አሕመድ ሽዴ
"የ2018 በጀት በከፍተኛ ሁኔታ የገቢ አቅምን ማሳደግ ላይ የተመሰረተ ነው" - ክቡር አሕመድ ሽዴ
(ዜና ፓርላማ) ሰኔ 24 ቀን፣ 2017 ዓ.ም፤ ለ2018 በጀት ዓመት የተዘጋጀው የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት በከፍተኛ ሁኔታ የገቢ አቅምን ማሳደግ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ አስረድተዋል፡፡
6ኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ41ኛ መደበኛ ስብሰባው በፌዴራል መንግስት የ2018 በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት ላይ በዝርዝር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ላይ በምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፤ የበጀት አቅርቦቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በተለይ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ለመስራትና የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ በቂ አለመሆኑን በስፋት ተነስቷል፡፡
የበጀት ድልድሉ ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የሕዝብና የቤት ቆጠራ መደረግ እንዳለበትም ተነስቷል።
በሀገሪቱ የሚገኙት የዲሞክራሲ ተቋማት የሚመደብላቸው በጀት አነስተኛ በመሆኑ ስራቸውን በነጻነት ለማከናወን እንደሚቸገሩም የምክር ቤቱ አባላት አንስተዋል፡፡
ለነዳጅ የሚደረገውን ድጎማ ማስቀረት እና በማዳበሪያ ላይ የተደረገው ጭማሪ የኑሮ ውድነቱን ሊያባብሰው እንደሚችል የምክር ቤቱ አባላት ያላቸውን ስጋት አንስተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ማክሮ ኢኮኖሚው የተረጋጋ የሚሆነው የመንግስት ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ሲያድግ እንደሆነ ገልጸዋል።
አዲስ የፋይናንስ ሥርዓት ነው የያዝነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በከፍተኛ ጉዳይ ገቢያችንን ማሳደግ የሞት የሽረት ጉዳይ ነው ብለዋል።
ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ታክስ ለጥቅል አገራዊ ምርት ያለው ምጣኔ ዝቅተኛ ነው፤ ይህንን በቀጣይ አራት ዓመታት በ4 በመቶ ማሳደግ ይኖርብናል ሲሉም ተናግረዋል።
ዘንድሮ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ከታክስ አንጻር የተሻለ ገቢ መገኘቱን አቶ አሕመድ ጠቁመዋል።
አዲስ የልማት ጥያቄ ለመፍታት ብለን ከብሔራዊ ባንክ የምንበደርበት አሰራር አብቅቷል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የተለያዩ የፋይናንስ ምንጮችን በመጠቀም የልማት ስራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
Copyright 2020 - All rights reserved. House of Peoples' Representatives