ሕወሓት እና ሸኔ  ስለ ሽብር የወንጀል  ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ አሟልተው መገኘታቸው ተገለጸ

(ዜና ፓርላማ) ፣ ሚያዚያ ፣ 28 ፣ 2013 ዓ.ም. ፣ አዲስ አበባ ፣  ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ( ሕወሓት) እና ሸኜ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ስለሽብር የወንጀል  ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ በሙሉ ማሟላታቸውን  የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት አስረድተዋል ፡፡

አምባሳደሩ ይህንን ያሉት  የሚኒስትሮች ምክር ቤት  ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና ሸኔ በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ  የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ነው ፡፡

 በድርጅቶቹ የተፈጸሙት ድርጊቶች የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 3 የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ በሙሉ የሚያሟሉ እንደሆኑ አምባሳደሩ አብራርተዋል ፡፡

 ድርጅቶቹ  ሲፈጽሙትና ሲያስፈጽሙት እንዲሁም አሁን ላይም በመፈጸም ላይ ያሉት ደርጊቶች  የሽብር የወንጀል ተግባር መሆናቸውንና  በሕብረተሰቡ ላይ እየደረሰ ያለውን የሽብር ተግባር ለማስቆም  እንደሆነ የውሳኔ ሃሳቡን ዓላማ  አምባሳደሩ አስረድተዋል ፡፡

የውሳኔ ሃሳቡ የሽብርተኛ ቡድንን የፋይናንስ አቅም ለማዳከም ፣ ሰላማዊ ዜጎች ከድርጅቶቹ ጋር እንዳይተባበሩ እና የሕግ አስከባሪ አካላት ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያብራሩት ፡፡

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በ 2011 ዓ.ም.  የ«ትግራይ ማዕከላዊ ወታደራዊ  ኮማንዶ » በማለት ሕገ-ወጥ የታጠቀ ኃይል እንዲደራጅ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው እንደተወሰነ ነው አምባሳደሩ የተናገሩት ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ወታደራዊ ኮማንዶውን ለማደራጀት እንዲመች በክልሉ የጸጥታ ቢሮ ስር  የሃይል ስምሪት ዘርፍ  የሚባል አዲስ የስራ ክፍል እንደተዋቀረም በውሳኔ ሃሳቡ ተጠቅሷል ፡፡

የተደራጀው ወታደራዊ ሃይል የክልል መንግስታት ሊታጠቁት የማይገባውን ሜካናይዝድ እና የቡድን መሳሪያ ስልጠና በመስጠት ለጦርነት ዝግጅት እንዳደረገ ነው በውሳኔ ሃሳቡ የተመላከተው ፡፡

ወታደራዊ ቡድኑ ታንክ ፣ መድፍ ፣ አየር መቃወሚያ እና ሮኬት ሳይታጠቅ እነኝህን መሳሪያዎች ማንቀሳቀስ እና መተኮስ የሚችል የሰው ሃይል ያሰለጥን እንደነበር በውሳኔ ሃሳቡ  ተብራርቷል ፡፡

ድርጅቶቹ አልቃይዳ ፣ ቦኮሃራም እና አይ.ኤስ.አይ ኤስ. አሸባሪ ድርጅቶች ከፈጸሙት  የሽብር ተግባር  የሚስተካከል ድርጊት ፈጽመው እያለ ፣ በሃገራችን ተደርጎ በማይታወቅ መልኩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታግተው ደብዛቸው የጠፋበት ፣ መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በተፈጸመበት ሁኔታ በሽብር ሳይፈረጁ መቆየታቸው  አግባብ እንዳለሆነ የምክር ቤቱ አባላት ገልጸው ፣ በአሸባሪነት መፈረጃቸው ትክክለኛ ውሳኔ  ነው ብለዋል ፡፡

«ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ድርጊት ሲፈጸም ለአለም - አቀፉ ማሕበረሰብ  ለምን በቂ ግንዛቤ አልተፈጠረም?» የሚል ጥያቄ  ከምክር ቤት አባል  ቀርቧል ፡፡

የፌዴራል ጠቅላ ዓቃቤ ሕግ ዋና ዓቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)  በበኩላቸው  ሌሎች ሀገራት የዓለም አቀፍ የሕግ ትብብር እንዲያደርጉ  የውሳኔ ሃሳቡ አጋዥ እንደሆነ ገልጸው ፣ የውሳኔ ሃሳቡን ለሌሎች ሀገራት በማስረዳት ግንዛቤ እንዲፈጠር ይሰራል ብለዋል፡፡

ውሳኔ ሃሳቡ ውሳኔ  ቁጥር 10 /2013 ሆኖ በአንድ ድምጸ-ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

በስሜነው ሲፋረድ