የወዳጅነት ቡድን
null የወዳጅነት ቡድን
የወዳጅነት ቡድንን ስለማቋቋም
1/ ምክር ቤቱ ከተለያዩ አገሮች አቻ የፓርላማ የወዳጅነት ቡድኖች ጋር ግንኙነት የሚያደርጉ የወዳጅነት ቡድኖችን ሊያቋቁም ይችላል፡፡
2/ እያንዳንዱ የወዳጅነት ቡድን ሊቀመንበሩንና ምክትል ሊቀመንበሩን ጨምሮ በምክር ቤቱ የሚመረጡ ከዘጠኝ እስከ አስራ አንድ የሚደርሱ አባላት ይኖሩታል፡፡
3/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን ተጠሪነት ለውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ይሆናል፡፡
4/ በዚህ አንቀጽ የተደነገገው ቢኖርም ምክር ቤቱ የሚያቋቁማቸውን የወዳጅነት ቡድኖች እንደሁኔታው በአህጉር፣ በክፍለ አህጉር ወይም በአካባቢ ደረጃ ሊያደራጅ ይችላል፡፡
የወዳጅነት ቡድን ተግባር እና ሃላፊነት
የወዳጅነት ቡድን የሚከተሉት ተግባርና ሃላፊነት ይኖሩትል፡-
1/ በአገሮቹ ህዝቦች መካከል ጠንካራ ወዳጅነት እና በጐ ግንኙነት እንዲኖር ጥረት ማድረግ፣
2/ ከአቻ ፓርላማዎች ጋር መተባበር፣ ልምድ መለዋወጥና ወዳጅነትን ማጠናከር፣
3/ አገራዊ ገጽታን መገንባት፣
4/ ስለሌላኛው አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ የተሟላ ግንዛቤ ማያዝ፣
5/ በኢትዮጵያና በሌላኛው አገር ያሉ የየወቅቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን መከታተልና የተሟላ ግንዛቤ መያዝ፣
6/ ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት ማከናወን፡፡
የወዳጅነት ቡድን አሰራር
1/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን ወዳጅነት የመሠረተበትን አገር የሚመለከት አጠቃላይ መረጃ እና ሌሎች ጠቃሚ ሰነዶችን በማሰባሰብ ለስራው በግብአትነት ይጠቀማል፡፡
2/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን ሥራውን በዕቅድ ይመራል ፣ በየጊዜውም የሥራ አፈፃፀሙን ይገመግማል፣
3/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን እንደአስፈላጊነቱ ስጦታዎችን ሊለዋወጥ፣ ጥናትና አውደ ጥናት ሊያካሂድ ወይም በአገር ውስጥና በውጭ አገር በተለያዩ ስብሰባዎች ተሣታፎ ያደርግ ይችላል፡፡
4/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን ሰነዶቹን በአግባቡ መያዝ እና ሥራውን በቃለ ጉባዔ መዝግቦ መያዝ ይኖርበታል፡፡
5/ እያንዳንዱ የወዳጅነት ቡድን ዕቅዱን እና የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ያቀርባል፡፡
6/ ማንኛውም የወዳጅነት ቡድን የራሱን የውስጥ የአሰራር ሥነ-ሥርዓት ሊያወጣ ይችላል፡፡
7/ በዚህ ደንብ ለኮሚቴ አባላት የተዘረዘሩ የሥነ-ምግባር ድንጋጌዎች እንደአስፈላጊነቱ ለወዳጅነት ቡድን አባላትም ተፈፃሚ ይሆናሉ፡፡
ከፓርላማ ህብረት ጋር ስለሚኖር ግንኙነት
1/ ምክር ቤቱ በዓለም አቀፋዊ፣ በአህጉራዊ እና በሌሎች የፓርላማ ዲፕሎማሲ ተግባራት ሊሳተፍ ይችላል፡፡
2/ በፓርላማ ህብረት መድረኮች ላይ የማሳተፉ አባላት ቁጥር በህግ መሠረት ወይም ከበጀት አንፃር እየታየ የሚወሰን ይሆናል፡፡
3/ በዚህ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ (2) መሠረት ምክር ቤቱን በቋሚነት የሚወክሉ አባላት በአፈጉባዔው አቅራቢነት በምክር ቤቱ የሚሰየሙ ሲሆን ተጠሪነታቸውም ለአፈጉባዔው ይሆናል፡፡
4/ አፈጉባዔው ምክር ቤቱን በጊዜያዊነት በመወከል በተለያዩ ስብሰባዎች የሚሳተፉ አባላትን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ይመርጣል፡፡
5/ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (3) እና (4) መሠረት ምክር ቤቱን በመወከል በተለያዩ መድረኮች የሚሳተፉ ልዑካን በተሳተፉበት ቦታ ሁሉ ስለጉዳዩ በቂ ዝግጅት ማድረግና አግባብ ካላቸው አካላት ዝርዝር መረጃ በማግኘት የአገሪቱን ጥቅም ያስጠበቀ እንዲሁም ምክር ቤቱ የገባቸውን ግዴታዎች እና ስምምነቶች በማክበር መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡
6/ በዚህ አንቀጽ መሠረት በተለያዩ መድረኮች የሚሳተፉ ልዑካን በዚህ ደንብ የተደነገጉ አግባብነት ያላቸው ሥነ-ምግባሮችና እንደሁኔታው በአንቀጽ 200 የተደነገገውን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
7/ በዚህ አንቀጽ መሠረት ምክር ቤቱን በመወከል በተለያዩ መድረኮች የሚሳተፉ ልዑካን ከተልዕኮ በኋላ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያቀርባሉ፡፡