null “Stand together, we can overcome our adversities”

“ለጋራ ጉዳዮች በጋራ ከቆምን፤ ሀገራዊ ችግሮቻችንን እንፈታለን”

  • ታገሰ ጫፎ፤ የኢፌዴሪ የሕ/ተ/ም/ቤት አፈ-ጉባዔ

የካቲት 18፣ 2012 ዓ.ም. አዲስ አበባ፤ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ክቡር ታገሰ ጫፎ ከዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን ጋር በተካሄደው የጋራ የምክክር መድረክ፤ “ለጋራ ጉዳዮች በጋራ ከተመካከርን እና ቁጭ ብለን ከተወያየን፤ ሀገራዊ ችግሮቻችንን እንፈታለን” አሉ፡፡

በክቡር አፈ-ጉባዔው ጽሕፈት ቤት ሰሞኑን በተካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ፤ በፖለቲካ አመራር የሚሳተፉ፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሀገራቸውን የሚያገለግሉ፣ የዕምነት ተቋማትን የሚመሩ የኃይማኖት አባቶች እና መላው የሀገራችን ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው በጋራ ለጋራ ጉዳዮች የሚቆሙበት ወቅት ላይ መደረሱን ራሳቸው አፈ-ጉባዔው ለውይይቱ ተሳታፊዎች አስገንዝበዋል፡፡

“ለልማት ሥራዎቻችንም ይሁን ለሌሎች የፖለቲካ ሥራዎች ሁሉ፤ ሰላም፣ ዕርቅ እና ይቅርታ ያስፈልጉናል፡፡ ሰው ተቀራርቦ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር መጀመሪያ ከውስጡ ይቅርታ፣ ሰላም እና ፍቅር ሎኖሩ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን ጥሩ ባሕልም፣ ዕምነትም ያለን ሕዝቦች ነን” በማለት፤ የዕርቀ-ሰላምን አስፈላጊነት አመላክተዋል፡፡

ሀገራችንን ወደተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር ካለብንም፤ በጋራ መቆም አማራጭ የሌለው ምርጫ መሆኑንም ክቡር ታገሰ አስረድተዋል፡፡ አንዳችን ሌላችንን በማዳመጥ፣ ክብር በመስጠት እንዲሁም በቅንነት በመነጋገር፤ ቀጣይነት ያለውን ሰላም እና ብልጽግና በሀገራችን ዕውን ማድረግ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ክቡርነታቸው በተጨማሪም፤ የሀገሪቱ የፖለቲካ ሥራዎችም ሆኑ ሌሎች የልማት ሥራዎች ሊሳኩ የሚችሉት፤ አስተማማኝ ሰላም እና ዕርቅ ሲረጋገጥ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር አያይዘውም፤ የርስ በርስ ነቀፌታዎቻችን ዳግም እንዳይከሰቱ በይቅርታ መንፈስ መቅበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በሀገራችን ላለፉት በርካታ ዓመታት የተሠሩት ጠቃሚ ሥራዎችም ጭምር በብዙ መልኩ የተለያዩ ትርጉሞች እየተለጠፉበት፤ ሕዝቡ አንድ ላይ እንዳይቆም እና ሀገር እንዳትጸና ለማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ማበርከታቸውን የገለጹት ክቡር አፈ-ጉባዔው፤ በሚያስተሳስሩን ትላልቅ ዕሴቶች ላይ ማተኮሩ ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽን ሰብሳቢ ካርዲናል ብፁዕ አባ ብርሀነኢየሱስ ደመረው በበኩላቸው፤ ፈጣሪ የተመሰገነ ይሁንና በሀገራችን ብዙ ቦታዎችን ስናይ፤ የሰላም፣ የዕርቅ እና የይቅርታ መንፈስ እየነፈሰ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በቤተሰብ፣ በመንደር፣ በክልል እና በሀገር ደረጃ እየመጣ በመሆኑም ደስ መሰኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም በፀሎት ከተጋ ወደ ሕሊናው እንደሚመለስ እና ከፈጣሪው ጋር እንደሚገናኝ ያስረዱት ብፁዕ ካርዲናሉ፤ በዚህ መልኩ አምላኩን የሚያከብር ሰው ደግሞ የእሱ ፍጡር የሆነውን ሰው እንደሚያከብርም አረጋግጠዋል፡፡

ሀገራችንን በጋራ እናሳድግ ብሎ ሕጻኑም፣ ወጣቱም፣ ትላልቁም በአንድነት እንደተነሳ መታዘባቸውን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናሉ፤ ሀገራችን የሰላም እና የዕርቅ መንገዱን በመከተል በተጀመረው የልማት ጎዳና እንደምትቀጥልም ዕምነታቸውን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ካርዲናል ብፁዕ አባ ብርሃነኢየሱስ፤ አምስት አባላትን ያካተተ ቡድን መርተው ነው ከክቡር አፈ-ጉባዔው ጋር የተወያዩት፡፡ እነርሱም፤ የአስተዳደር እና አጋርነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ጥበበ የማነብርሃን፣ የፍትሕ እና ዕርቅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ልዑል በዕደማርያም መኮንን፣ የመረጃ መሰብሰብ እና መተንተን ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታምሩ ለጋ፣ የእውነት አፈላላጊ እና በደል አጣሪ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ታምራት ኪዳነማርያም እንዲሁም የኮሚሽኑ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት አለማየሁ መሆናቸውን መረዳት ተችሏል፡፡

ከተቋቋመ ገና የአንድ ዓመት ዕድሜ ብቻ ያስቆጠረው የዕርቀ-ሰላም ኮሚሽኑ፤ ሀገራዊ ችግሮችን በሀገራዊ ስልት ለመፍታት ታቅዶ ከብዙ ምክክር በኋላ እንደተመሠረተ ይታወቃል፡፡

አሥራት አዲሱ

  የምክር ቤት ፀሐፊ