null 49 institution having serious problems and 11 institutions Unable to comment should hurry out of their problems.

የጎላ ችግር ያለባቸው 49 ተቋማት እና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው 11 ተቋማት ካሉበት ችግር ፈጥነው እንዲወጡ ተባለ፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2011 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ ከባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም የጋራ ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

ሪፖርቱን ያቀረቡት የቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጀምበሩ ሞላ በበጀት ዓመቱ በባለድርሻ አካላትና በኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች የታዩ ጥንካሬዎች፣ ዕጥረቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ መፍትሔዎች፣ መሻሻል ያለባቸው እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በተሰሩ ስራዎች የተገኙ ውጡቶች እንዲሁም ለቀጣይ በጀት ዓመት የተያዙ የትኩረት አቅጣጫዎችን ያካተተ  ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባለድርሻ መ/ቤቶች የዓመቱን ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በወቅቱ የላኩ ቢሆንም ከቋሚ ኮሚቴ የሚሰጣቸውን የአፋጻጸም ግብረ መልስና አቅጣጫ እንዲሁም በዋና ኦዲተር የተሰጣቸውን የኦዲት ግኝትና ማሻሻያ ሪፖርት በአዎንታ ተቀብለው ስራ ላይ አለማዋልና በዕቅድም ካለመምራት ባሻገር የተቆጣጣሪነትና ህግ የማስከበር ስልጣን ያላቸው ም/ቤቱ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ገንዘብ ሚኒስቴር ከአምና የተሸለ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢገኙም አሁንም ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንፃር ውስንነት እንደሚታይባቸው ተነስቷል፡፡

ፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዲቢሶ በበኩላቸው አልፎ አልፎ ኦዲት ግኝት ዘገባዎች ትኩረት የሚሹ ሆኖ ሳለ የሚዲያዎች የዋና ኦዲተር ማጠቃለያ ሃሳብና ለቀጣይ የሚቀመጡ አቅጣጫዎችን በተሟላ መንገድ ለህዝቡ በጥራትና በጥልቀት ተደራሽ ማድረግ ሲገባቸው  ቁንጽል ሀሳቦችን እየዘገቡ በመሆናቸው ለቀጣይ የሚስተካከልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል ብለዋል፡፡

ዋና ኦዲተሩ አክለውም ም/ቤቱ የኦዲት ግኝቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ይበል የሚያሰኝ እደሆነና አሁንም ከሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ጋር ተያይዞ በዩኒቨርስቲዎች የተመን ጉዳይ እልባት ካላገኘ ቀጣይ የኦዲት አካል የመሆኑ እድል ሰፊ እንደሆነ እና በቀጣይም ለረጅም ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት የሚሰሩ  መሆናቸውን ተገናግረዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴ በዘንድሮ በጀት ዓመት በተሰራው ስራ ከፍተኛ ብክነት የሚታይባቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ፊዚብሊቲ ሳይጠና እንዳይጀምሩ መከልከላቸው እና በፊት የማይነኩ የመንግስት ተቋማት ለኦዲት ግልጽ መደረጋቸው ለውጡ እንዳለ የሚያሳይ ቢሆንም በፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2010/2011 ኦዲት አስተያየት መሰረት ሂሳባቸው የጎላ ችግር ያለባቸው 49 ተቋማት እና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው 11 ተቋማት ካሉበት ችግር እንዲወጡ ለማድረግ የተጠራቀመውን ተሰብሳቢ ሂሳቦችን መፍትሄ እንዲያገኙ የህግ አሰራር ማሻሻያ በማድረግ ማብቃትም እዳለባቸው በትኩረት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም በርካታ የመንግስትና የህዝብ ሃብት በአያያዝ ስርዓት ማጣት፣ አወጋገድ ስርዓት አለመኖር እና የአመራሮች ውሳኔ ያለመስጠት ችግር ለከፍተኛ ሲጋለጥ መቆየቱን አንስተው በተለይ በኬሚካልና በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይ ችግሩ ሰፊ በመሆኑ የተለየ ትኩረት እንዲያገኙ የፎረም አባላት በጋራ አቅደው መስራት እንዳለባቸውም ተነስቱል፡፡           

ም/ቤቱም አብዛኛዎቹ የባለበጀት መ/ቤቶች የሀብት አስተዳደራቸው መንግስት ከዘረጋው አሰራር ያፈነገጠ በመሆኑ እና የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ በአስፈጻሚ ተቋማት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ የሚያስገድድ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አጽድቆ የጠ/ሚኒስትር አስተያየት እንዲሰጥበት እንደሚጠበቅና ውሳኔ ሃሳቡም አምስት ነጥቦችን የያዘ ሲሆን ለአብነትም አሰራርና ህግን ባልተከተሉ ወጪዎች አስቸኳይ እርምጃ የሚወሰዱበት፣ የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲመለስ የሚያደርግ አሰራር የሚዘረጋበት እና አሰራርን በጣሱ ኃላፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የሚደነግግ መሆኑን የገለጹት በቋሚ ኮሚቴ ን/ሰብሳቢ የሆኑ ወ/ሪት ወይንሸት ገለሶ ናቸው፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ባለድርሻ አካላትና ባለበጀት መ/ቤቶች የዋና ኦዲት መ/ቤት ግኝት መሰረት በማድረግ ከፍተኛ የኦዲት ጉድለት የተገኘባቸው የመንግስት ሃብትንና ንብረት እንዲያስመልሱ፣ እዲያስጠይቁ እንዲሁም የአሰራር ችግሮችን እዲያስተካክሉ በማድረግ ብሎም ህግን መሰረት ያደረገ ግልጸኝነት ያለበት አሰራር እንዲኖር ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አሳስቧል፡፡