null A human rights violation is still continued on prisoners.

በህግ ቁጥጥር ስር በዋሉ ታራሚዎች ላይ አሁንም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ እንደሆነ ተገለጸ

ይህ የተገለጸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልል ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና እንባ ጠባቂ ተቋም ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን በጎበኘበት ወቅት ነው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባህርዳር ቅርንጫፍ ባገኙት መረጃ ታራሚዎችን ያለበቂ ምክንያት ከአንድ ማረሚያ ቤት ወደ ሌላ  ከማዘዋወር ባለፈ አሁንም በክልሉ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ዘንድ በዜጎች ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይም ወጣት ጥፋተኞችን በትምህርትና በስነምግባር አንፆ ወደ ቤተሰቦቻቸው ከመመለስ ይልቅ ለረጅም ጊዜ ከአዋቂ ታራሚዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲታረሙ በመደረጉ ወጣቶች ለከፋ እንግልትና ለስነ-ልቦና ጉዳት እየተጋለጡ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ቡድን ተገንዝቧል፡፡

ተጠርጣሪ ወንጀለኛች በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ቀርበው ሳይዳኙ ለብዙ ወራቶች በደረቅ ጣቢያ አንዲቆዩ መደረጉ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸው እየተጣሰ እደሆነም የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መረዳት ችሏል፡፡

የሁለቱ ተቋማት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ የህግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀትና የመዋቅር ችግሮች እንደነበሩባቸው የቋሚ ኮሚቴ ቡድኑ ተረድቶ አሁን ላይ ተቋሞቹ  በውስጣዊና በውጫዊ ችግሮች ምክንያት ለዜጎች ተገቢውን አገልግሎት እየሰጡ ነው ማለት እንደማይቻል አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባህርዳር ቅርንጫፍ የጂኤጂ ምደባ፣ የግብዓት አቅርቦት አና የአመራር አቅም ውስንነትቶች እአንዳሉ የገለጹት የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በአቤቱታ አቀራረብና በሰነድ ምርመራ ሂደት ላይም በርካታ ችግሮች እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

የእንባ ጠባቂ ተቋም ባህርዳር ቅርንጫፍ ሰራተኞች በበኩላቸው መስሪያ ቤቱ በመንግስት ደረጃ ትኩረት የተነፈገው እንደሆነ ገልጸው የህግና የመዋቅር ማሻሻያ፣ እንደሁም የደመወዝና የጥቅማጥቅም ማስተካከያ ተደርጎ ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት መስጠት ካልተቻለ ተቋሙ መታጠፍ ወይም መፍረስ አለበት ሲሉ ሃሳብ አአንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል የቋሚ ኮሚቴው አባላት በክልሉ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ያሉበትን ሁኔታ ቀድሞ በመድረስ የሰብአዊ መብት ኮሚሽ ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቱ ያከናወነውን ተግባር አስመልክቶ ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባህርዳር ቅርንጫፍ ኮሚሽነር አቶ አበረ ሙጬ የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት በጸጥታና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች እንደ ተቋም ቀድሞ በመግባት የተከናወነ ተግባር አንደሌለ ተናግረዋል፡፡

የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እንባ ጠባቂ አቶ ጋሻነው ደሴ በበኩላቸው ተቋሙ ከበጀት አንስቶ እስከ ማቴሪያል ግብዓት በርካታ ችግሮች  እንዳሉበት ገልጸው በሌላ በኩል ተቋሙ ይታጠፍ ወይም ይፍረስ የሚል ከሰራተኛው የተነሳው ሀሳብ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ መፍረስ ደረጃ ላይ የሚያደረስ ነባራዊ ሁኔታ አለመኖሩን የተናገሩት አቶ ጋሻነው ለአሰራር እንቅፋት የሆኑ ቁልፍ ማነቆዎች ግን በአስቸኳይ መቀረፍ አለባቸው  የሚለው ገዢ ሀሳብ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው በሁለቱ ተቋማት የሚስተዋሉ ስር የሰደዱ ችግሮች በአስቸኳይ ተቀርፈው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቋማዊ ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው እና ዜጎች ተገቢውን አገልግሎት ሊያገኙ እንደሚገባ  አሳስበዋል፡፡