null Commitees of the House held public heareing on communication services draft bill.

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ ላይ ይፋ የህዝብ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት ይህ አዋጅ የኢትዮጵያ ኮሚኒዩኒኬሽን ባለስልጣንን ለማቋቋምና ወደ ስራ ሲገባም ሊያሰሩት የሚችሉ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች መቀመጣቸውን ገልጸው ባለስልጣኑ የተለያዩ ሶስት ዘርፎችን እንደሚቆጣጠር እነሱም የቴሌ ኮሚዩኒኬሽን፣ የፖስታ አገልግሎትና የብሮድ ካስት ዘርፎች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ እነዚህን ዘርፎች አንድ ላይ እንዲቆጣጠር ያስፈለገው ተቋሙ ወደ ስራ ሲገባ ውድ የሆነውን የሃገር ሃብት ፍሪኩየንሲ የመቆጣጠር  ስራ ስለሚሰራ መሆኑንና የኮሚዩኒኬሽን ዘርፎችን በአንድ ላይ መጠቅለል ስላስፈለገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

አያይዘውም ከሌሎች አገራት ባገኙት ልምድ ባለስልጣኑ ነጻና ገለልተኛ እንዲሆን ማስፈለጉንና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ ዓላማ ተወዳዳሪ የገበያ ሥርዓትን በማበረታታት፣ የተጠቃሚዎችን ተደራሽነትና ፍላጎት ያሟላ፣ ጥራቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ አስተማማኝ እና ኢኮኖሚያዊ አቅምን ያገናዘበ የኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ እንዲስፋፋ ማድረግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

 

ከተሳታፊዎች ከተነሱ አስተያየቶች ውስጥ መቅደም ያለበት የኢንቨስትመንት ህጉ ነው ስለዚህ ማሻሻያ ቢደረግበት፣ የአዋጁን አንቀጽ 31 የመሬትና ህንጻ ስለመጠቀም በሚመለከት አንዳንድ አገላለጾች ቢስተካከሉ፣ አንዳንድ አገላለጾች ግልጽ የሆነ ትርጉም እንዲኖራቸው ቢደረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

 

ከቋሚ ኮሚቴዎቹ በአጠቃላይ በትርጉም ደረጃ መታየት አለባቸው የተባሉ ነገሮች ዝግ ባይደረጉና ቢታዩ፣ በትርጉም ደረጃ ክፍተት የሚፈጥሩ ቃላቶች መታየት አለባቸው፣ ከአንቀጽ 31 ጋር ተያይዞ ከመሬት አጠቃቀምና ከህንጻ ጋር ያለው የግለሰብ ሆነ የተጠቃሚዎችን መብትም ሳይጋፋ ከህግ አኳያ በማየት የሚስተካከልበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡

 

ከገበያ ድርሻ በተያያዘ፣ ገለልተኛ የሚለውን ሃሳብ ግልፅ ቢደረግ፣ ከቦርድ አባላት ጋር ያለው 7 አመት የጊዜ ገደብ የሚለው በ5 አመት ቢስተካከል፣ የጥቅም ግጭት በሚመለከት ያለውም መፈተሽ እንዲሁም ወደ ህብረተሰቡ ሲወርድ የማያሻሙ ቃላቶችን መጠቀምና ማስተካከል ቢቻል የተሻለ አዋጅ እንደሚሆን አንስተው በደንብና በመመሪያ የሚመለሱት እንዳሉ ሆነው መታየት ያለባቸውን ግን አስተካክለው እንዲያቀርቡ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

ክቡር ሚኒስትሩ ከቋሚ ኮሚቴዎቹና ከሌሎቹም ባለድርሻ አካላት የተነሱ አስተያየቶችን እንደ ግብአት ተጠቅመው አስተካክለው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡