null Committee of the House discussed on 2009 buget oudit finding of the Ministry of customs and revenue.

ሚያዝያ 2 ቀን 2011 ዓ.ም!- ኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የገቢዎች ሚኒስተር የ2009  ዓ.ም የሂሳብ ግኝት ላይ ተወያይቷል፡፡

የኢፌዴሪ ገቢዎች ሚኒስተር ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አበቤና ሌሎች የስራሃላፊዎች የጉምሩክን በሚመለከት ወደ 2.5 ቢሊየን ብር በጉድለት የተገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 1.07  ቢሊየን መሰብሰቡንና እርምጃ መወሰዱን ገልጸው ቀሪውንም በሂደት የሚያስተካክሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሃገር ውስጥ ታክስን በሚመለከት 11 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ያሉ ሲሆን 8.1 ቢሊየን ብር ሊሰበሰብ እንደሚገባ በኦዲት የቀረበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 1.1 ቢሊየን ተሰብስቦ ቀሪው በሂደት ላይ መሆኑን እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን አብራርተዋል፡፡

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ሚኒስተር መስሪያ ቤቱ የተሟላ ባይሆንም እያደረጉ ያለው የማስተካከያ እርምጃ ጥሩ መሆኑን አንስተው ይሰብሰብ ከተባለው ግብር ውስጥ ያልተሰበሰቡ መኖራቸው፣ ከበጀት አጠቃቀም ጋር በርካታ ግኝቶች መኖራቸው፣ ያለአግባብ የተከፈለ የትርፍ ሰአት ክፍያ፣ ከተሰብሳቢ ጋር ተያይዞ በወቅቱ ያልተወራረደና ከማን እንደሚሰበሰብ ግልጽ ያልሆነ ሂሳብ፣ ተከፋይን በሚመለከት በወቅቱ ያልተወራረደ ሂሳብ መኖሩንና ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

የተወረሱን ብረቶችንም በወቅቱ መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግና በተሰጠው ስልጣን አግባብ እርምጃዎችን መውሰድ መቻል እንዳለበት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ተቋማት ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡ መስሪያ ቤቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግና የክትትልና ቁጥጥር ስራውም አብሮ ማሳደግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በጉምሩክ አዋጅ መሰረት የመጫኛና ማራገፊያ ባህር ትራንዚት ኢንሹራንስ በትክክለኛ በቀረጥና ታክስ ማስከፈያ ዋጋ ላይ ያለመካተቱ፣  በቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶች በኩል ወደ ሃገር ውስጥ ገብቶ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ተወስኖባቸው ያልተከፈለባቸው መኖራቸው፣  የቀረጥ ሂሳብ መሰብሰቢያ ደረሰኞች የገቢና ወጪ ቁጥጥር ስርአት የሌለውና የማይመዛዘን መሆኑ እንዲሁም የተመደበለትን የካፒታል በጀት በአግባቡ ስራ ላይ አለማዋሉና ሌሎችንም ጉዳዮች አንስቷል፡፡

መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት አንጻር ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ተቋም በመሆኑ ከሌሎቹ ተቋማት ጋር በመተባበር የተቋቋመለትን አላማ በተገቢው ማሳየት ከቻለ አገሪቱ ከድህነትና ከሃላቀርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደምትላቀቅና በዚህም መሰረት የሂሳብ ግኝት በማረም ቀልጣፋ ውጤታማና ስኬታማ ስራዎች ካልተሰሩ ኢኮኖሚው ግቡን እንዳይመታ የሚያደርግ በመሆኑና ከፍተኛ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል በማወቅ መስሪያ ቤቱ ጥብቅ የሆነ የክትተልና የቁጥጥር ስርአት በማዘጋጀትና የውስጥ ኦዲት አቅምን በማጠናከር ከኋላቀር አሰራር በመላቀቅ ወደ ዘመናዊ መሸጋገር እንዳለበትም ቋሚ ኮሚቴው አንስቷል፡፡