null Committee of the House evaluated 2019 budget 9 months performance report of the Federal Integrated Infrastructure Development Coordinating Agency.

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 9 ቀን 2011 ዓ.ም  የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ የ2011 በጀት አመት የ9 ወር ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡

 በውይይቱ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር  አቶ አልማው መንግስት እንደገለጹት ለመሰረተ ልማት ስራዎች ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ሰነድ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው የመሰረተ ልማቶች የቅንጅት ትግበራ ፈቃድ አለመሰጠቱንና ለዚህም ምክንያቱ አስፈጻሚ አካላትን ለማስገደድ የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ አለመጽደቁ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በበጀት አመቱ 75 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን 55ቱን ክትትልና ድጋፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች ጋር የተያያዙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ኢትዮ ቴሌ ኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይልና ለኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽን ክትተልና ድጋፍ በማድረግ አስፈጻሚ አካላት ለሚያነሷቸው የተለያዩ ችግሮች መፍትሄ መሰጠቱንና ከተቋሙ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ደግሞ ለሚመለከተው አካል ሪፖርት እንዲቀርብ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኤጀንሲው ከሁሉም የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር አንድ ሀገራዊ የተቀናጀ የመሰረተ ልማት ዕቅድ መዘጋጀቱ እና ከአስፈጻሚ አካላት ጋር የተናበበ ዕቅድ ተዘጋጅቶ መግባባት ላይ መድረሱ በጥንካሬ አንስቷል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን ከመታገል አኳያ የተሰሩ ስራዎች፣ የተለያዩ ተግባራትን ለማከናወን የሚረዱ የተለያዩ ሰነዶች መዘጋጀታቸው፣ ለሰራተኞች የተሰጡ የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች እንዲሁም በዘርፈ ብዙ የተሰሩ ስራዎች በጥሩ ጎን አይቷል፡፡

በሌላ በኩል ተቋሙ የካሳ አሰራር ከመዘርጋት፣ የነጠላ ዋጋ ወጪ ከማድረግ እና የተነሺዎችን መልሶ ማቋቋሚያ ሰነድ ዝግጅት ከንድፈ ሃሳብ የዘለለ አለመሆኑ በእጥረት አንስቶ የሰነድ ዝግጅቱ ፈጥኖ አልቆ ወደ ስራ የሚገባበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁማል፡፡

በነባርና በአዲስ ፕሮጀክቶች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠል እልዳለበትና ከበጀት አጠቃቀም አኳያ በተለይም የካፒታል በጀት አፈጻጸሙ ዝቅተኛ በመሆኑ የተመደበውን በጀት ለታለመለት አላማ እንዲውል መስራት  እንደሚያስፈልግ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፤ በቀጣይም ግብረ መልሶቹን በመጠቀም የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡