null Committee of the House reported that inability to prevail rule of law is the key problem of development in the Harar and Diredawa cities.

የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ አለመቻል ለድሬዳዋና ሐረር ከተሞች እድገት  ቁልፍ ተግዳሮት መሆኑን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፣

ቋሚ ኮሚቴው ሰሞኑን በድሬዳዋና ሐረር ከተማ አስተዳደሮች ተገኝቶ በስራ ዕድል ፈጠራና በምግብ ዋስትና ዘርፎች፣ በመሬት ልማትና አስተዳደር፣ በቤት ልማት ስራዎች፣ በመሰረተ ልማት አቅርቦት ጥራትና ተደራሽነት፣ በከተማ ፅዳትና ውበት፣ በኮንስትራክሽንና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የተከናወኑ ተግባራትን ተመልክቷል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ከድር ጁዋር የከተማውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ አስመልክተው እንደተናገሩት በበርካታ ዘርፎች የከተማዋ እድገት ወደኋላ እየተመለሰ መሆኑን አንስተው ለዚህም ዋና ዋናዎቹ ችግች ፍትሃዊ የገቢ ክፍፍል አለመኖርና የመልካም አስተዳደር እጦት ናቸው ብለዋል፡፡

ድሬዳዋ በታሪኳ ሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተቻችለውና ተከባብረው የሚኖሩባት የፍቅር ከተማ ሆና ሳለች በአሁኑ ወቅት ለድሬዳዋ ከተማ በማይመጥን ሁኔታ በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ የፀጥታ ችግር እየተከሰተ እንደሆነና ድርጊቱን አንዳንድ የፀጥታ አስከባሪዎችና አመራሮች ጭምር የሚሳተፉበት መሆኑ ችግሩን የበለጠ አስከፊ አድርጎታል ብለዋል ምክትል ከንቲባው፡፡

ከህገ-ወጥ ግንባታ መስፋፋት ጋር ያለውን አስመልክተው አቶ ከድር ሲገልጹ ድሬዳዋ ከተማ ላይ ያለው የህገ-ወጥ ግንባታ ሽፋን እጅግ ከፍተኛ እንደሆነና ለዚህም ዋናው ችግር አመራሩ ህግን ከማስከበር ይልቅ በህገ-ወጥ ተግባራት ላይ የሚሳተፍ መሆኑ እንደሆነ አንስተው በአሁኑ ወቅት ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና የህግ ማስከበር ስራውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግብረ-ሃይል አደራጅተን ወደ ተግባር ገብተናል ብለዋል፡፡

ከስራ እድል ፈጠራ አኳያ በርካታ ማህበራትን ብናደራጅም የስራ ፈላጊው ቁጥር ከከተማው አቅም በላይ በመሆኑ የመንግስት ድጋፍ ያስፈልገናል ያሉት አቶ ከድር የብድር አሰጣጥ መመልመያ ነጥቦቹም ለድሃ የሚከብዱና ለሃብታም የሚያመቹ በመሆናቸው መንግስት እንደገና ሊፈትሻቸው ይገባል በማለት ተናግረዋል፡፡

የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት የመኖሪያ ቤት ችግርን ከመፍታቱም ይልቅ የሚፈጥረው የስራ እድልና ለቴክኖሎጅ ሽግግር የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በመንግስት በኩል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አቶ ከድር አንስተው ፕሮጀክቱ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አኳያ ከተማ አስተዳደሩ ባለው አቅም 358 ክፍሎችን የያዙ 11 ብሎኮች እየገነባ እንደሆነና ነገር ግን ቀጣይነቱን ለማረጋግጥ የፌደራል መንግስት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

ሐረር ከተማ ላይም በተመሳሳይ ላለው ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለመሰረተ-ልማትና ለመልካም አስተዳደር እጦት እንዲሁም ለፀጥታ ችግርና ለህገ-ወጥነት መስፋፋት ዋናው ችግር ዘረኝነት እንደሆነ ከአመራሩና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በተደረገ ውይይት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በሰጠው አስተያየት እንዳለው በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ካለው ሰፊ የስራ አጥ ቁጥር አንፃር የተለየ ዕቅድ እና የትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥ መሰራት እንደሚገባ ጠቁሞ አመራሩ ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆን ይጠበቅበታል ብሏል፡፡

ከመሬት ልማትና አስተዳደር ስራዎች አንፃር በከተማው ነዋሪ ዘንድ ያለውን ከፍተኛ ቅሬታ ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የመሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ እና መረጃ ተቋምን በአግባቡ ከማደራጀት ጀምሮ የይዞታ ማረጋገጥና የመመዝገብ ስራውን በማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት  ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

የድሬደዋና ሐረር ከተሞች ከሰላም እና ደህንነት አኳያ ለሌሎች የሀገራችን ከተሞች ምሳሌ የነበሩ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ይህ እሴት እየተሸረሸረ ስርዓት አልበኝነትና ዘረኝነት እየነገሰ መምጣቱን ከህብረተሰቡ ጋር በነበረው ውይይት ማረጋገጡን የገለጸው ቋሚ ኮሚቴው  የሚመለከተው አካል ሁሉ ተቀናጅቶ በመስራት ከተሞቹን ወደነበሩበት የሰላም፣ የፍቅር እና የመቻቻል  ባህል መመለስ ያስፈልጋል በማለት አስገንዝቧል።

የሐረር ከተማ ለልማት ከቦታቸው የተነሱ 46 የሚሆኑ አርሶ አደሮች የተሰጣቸውን ካሣ ከማጥፋታቸው በፊት አደራጅቶ ቦታ እንዲሰጣቸው በማድረግ  G+7 ህንፃ እየገነቡ መሆኑ ለሌላ አካባቢም አርአያ የሚሆን ተግባር መሆኑን ያነሳው ቋሚ ኮሚቴው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ፣ የመሬት ወረራ እና ህገ-ወጥ ግንባታ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር አፈታት፣ የፅዳትና ውበት ስራዎች ተገቢውን ትኩረት ማግኘት ይኖርባቸዋል በማለትም አመላክቷል፡፡

 ቋሚ ኮሚቴው አክሎም በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ከላይ እስከታች ያለው አመራር በተለይ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር፣ በመልካም አስተዳደር፣ በሰላምና ፀጥታ ስራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አስገንዝቦ በህብረተሰቡ እና በአመራሩ መካከል ተቀራርቦ በመስራት በኩል የሚታዩትን ክፍተቶች ማጥበብ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን የከተሞቹን እድገት ማፋጠን ይገባል በማለት አሳስቧል።