null Committee of the House visted Somali regional state.

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና፣ አርብቶ አደርና አከባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሶማሌ ክልል ቸረር ዞን ደጋሀቡር ወረዳና በአመድሌ የእንስሳት ማቆያ የመስክ ምልከታ አካሂዷል፡፡

አርብቶ አደሩ እንስሳትን ከማርባት በተጨማሪ በእርሻ ስራ ተሰማርቶ የምግብ ዋስትናውን በማረጋገጥ በተለይ በደጋሐቡር ወረዳ ፈልፈል ቀበሌ ለእነስሳት መኖና ለእርሻ የሚሆን መቶ ሔክታር ለመቶ አባወራዎች ለመስጠትና አልምተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የክልሉ መንግስት መጀመሩን ቋሚ ኮሚቴው  ተመልክቷል፡፡ 

ኮሚቴው ያናገራቸው አርብቶ አደሮችም እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን የገለፁ ሲሆን፤በስፋት በስራው ላይ ለመሰማራት የእርሻ መሳሪያና የዘር አቅርቦት እንደሚያስፈልጋቸው አንስተዋል፡፡

የአርብቶ አደሩን የጤና ደረጃ ለማሻሻል በወረዳው 6 ጤና ጣቢያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸው እንደ ጥሩ ጎን ቢነሳምየመድኃኒት አቅርቦት ዕጥረት ከፍተኛ መሆኑ፣ ጤና ጣቢያዎች ካላቸው ርቀትና ከወረዳው አቀማመጥ አንጻር ሲታይ አንድ አምቡላንስ ብቻ መኖሩ ለድንገተኛ ህክምና ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ችግር እንደሆነ  ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ መልስ አመላክቷል፡፡

በወረዳው የሚገኘው ሆዳሌ ትምህርት ቤት የቤተ-መፅሐፍት፣ ቤተ-ሙከራ፣ በአንዳንድ የትምህርት ዓይነቶች የመምህራን እጥረት እና ከፍተኛ የክፍል ጥበት መኖሩን  ቋሚ ኮሚቴው  በመስክ ምልከታው ገምግሟል፤ በተጨማሪም በአንድ ቅጥር ግቢ የቅድመ መደበኛ ትምህርት እስከ መሰናዶ በአንድ ላይ የማስተማሩን  ሂደት እና በአንድ ዳይሬክተር ብቻ  እንዲመራ መደረጉ   ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ ቋሚ ኮሚቴው  ጠቁሟል፡፡

በወረዳው ካለው ማህበረሰብ አብዛኛው አርብቶ አደር በመሆኑ ለትምህርት ያለውም ፍላጎት ዝቅተኛና የተማሪዎች መጠነ መቆራረጥ ሂደትም ከፍተኛ መሆኑ እንደ ድክመት ገምግሞ የግንዛቤ ስራም እየተሰራ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ተብራርቷል፡፡ 

ቋሚ ኮሚቴው ሌላው የተመለከተው በክልሉ 564 ካሬ መሬት ላይ ያረፈና በአንዴ 32 ሺህ እንስሳትን መያዝ የሚችል የአመድሌ የእነስሳት ማቆያ ፕሮጀክት ተጀመረው 2007 . ሲሆን በዲዛይን፣ በጥራት ጉድለትና የውሃ ስራው ባለመጠናቀቁ አገልግሎት እየሰጠ እንዳይደለ ታውቋል፡፡

አኬር ኮንስትራክሽን ለቆ በመሄዱ ለክልሉ ልዩ ፖሊስ ኮንስትራክሽን ተሰጥቶ እየተሰራ ያለው የእነስሳት ማቆያው ከሚጠበቀው በላይ መዘግየቱ አርብቶ አደርና የእንስሳትን ተዋፅዖ መሰረት በማድረግ ህይወቱን የሚመራው ማህበረሰብ ተጠቃሚም እያደረገ እንዳልሆነም አንስተው በፕሮጀክቱ ሲሰሩ የነበሩ 350 ሰራተኞችም የአራት ወራት ደሞዛቸው ያለመከፈል ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል ተብሏል፡፡    

የውሃ ተደራሽነት በወረዳው ካለው 10 ቀበሌ 8 የተዘረጋ ቢሆንም ተጠቃሚ እየሆኑ እንዳይደለ  እና ለክልሉ መንግስትም በየጊዜው ቀርቦ ምንም ምላሽ ያልተሰጠበት ሲሆን የአንድ ወረዳ ብቻም ሳይሆን ችግሩ አጠቃላይ የክልሉ መሆን  የክልሉ ኃላፊዎች ለቋሚ ኮሚቴው ገልፀዋል፡፡ ችግሩ ከክልልም አቅም በላይ በመሆኑ የተቆፈሩ 56 ጉድጓዶች አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላትም ጋር እየተሰራ  ነው፡፡