null Ethiopian Wild life Conservation Authority should give attention to protect animals in danger.

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ህልውናቸው ለአደጋ የተጋለጡ እንስሳትን መታደግ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌድሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና አርብቶ አደር እና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን የ2011 በጀት አመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ በባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ በኤረር እና ጎበሌ ሸለቆዎች የሚደረገው የመሬት ወረራ በአሁኑ ወቅት መቆሙና የተወሰነ አካባቢም ከሰው ንኪኪ ነፃ መሆናቸውን፣ በአብጃታ-ሻላ ሐይቆች ብ/ፓርክ የአሸዋ ቁፋሮን ሙሉ በሙሉ እና አስከፊ የደን ጭፍጨፋን ለመቆጣጠር መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በአዋሽ ብ/ፓርከ ውስጥ በሕገ- ወጥ መንገድ ሰፍረው የነበሩ 43 አባወራዎች በቅንጅት የማስወጣት እና በፓርኩ ሰሜናዊ ክፍል የነበረው የዘምባባ ዛፍ ጭፍጨፋን የመቆጣጠር ስራ ተከናውኗል፡፡

በአብጃታ ሻላ፣ በሰንቅሌ፣ ቃፍታ ሽራሮ፣ አላይደጌ አሰቦት፣ አዋሽ፣ እና ባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ከወረዳው አካላት እና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት 5,320 ሄ/ር መሬት ከደን ጭፍጨፋ ነጻ የማድረግና በነጭሳር ብ/ፓርክ 100 ሄክታር መሬት ደን ጭፍጨፋ ዘመቻን የማስቆም ስራ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡

ባጠቃላይ ባሌ ተራራዎች፣ ሃላይደጌ አሰቦት፣ ነጭ ሳር፣ ስንቀሌ፣ አዋሽ፣ ሰሜን ተራራዎች፣ቃፍታ ሸራሮ፣ አብጃታ ሻላ ሓይቆች ብ/ፓርኮችን እና ባቢሌ ዝሆኖች መጠለያን ከእርሻና ሰፈራ ነጻ ለማድረግ በተካሄደው የተቀናጀ የህግ ማስከበር ስራዎች 452 ህገ-ወጦች ከፓርኮቹ እንዲወጡ መደረጉን እና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች መሰጠቱን በሪፖርታቸው አሳውቀዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ባለስልጣኑ የእቅድ ዝግጅት እና ፈጻሚን በማዘጋጀት የተሰሩ ስራዎች፣ ከሕብረተሰቡ ተጠቃሚነት አንጻር በኢኮ ቱሪዝም የተከናወኑ ተግባራት የተካሄዱ የንቅናቄ መድረኮችና የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል ህገ-ወጥ ሰፈራ፣ አደን እና ጭፍጨፋን ለመከላከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በሚገባ ማሳደግና የኔነት ስሜት መፍጠር፣ ህልውናቸው ለአደጋ የተጋለጡ እንስሳትን በሚመለከት መታደግ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎች፣ የስራ እድል ፈጠራ፣ ህገ-ወጥ ዝውውር አደንና ንግድ፣ የኦዲት ግኝቶችን በወቅቱ ማረም እንዲሁም በአጠቃላይ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴው የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተርና ሌሎች የስራ ሃላፊዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አስተያየቶችንም ተቀብለው በቀጣይ እንደሚያስተካክሉ ገልጸዋል፡፡