null Federal Urban Land and Related Property Registry and Information Agency’s working performance is not efficient.

የፌደራል መሬትና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የስራ አፈጻጸም የተጠበቀውን ያህል አይደለም ተባለ፡፡

ጥር 20/2011 ዓ.ም ኤጀንሲው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2011 በጀት የግማሽ አመት የሪፖርት አፈጻፀሙን አሰምቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አምና ባካሄደው ግምግማ ተቋሙ ከአደረጃጀቶች ጋር ታች ወርዶ ከመስራት አኳያ በጣም ዝቅተኛ እንደነበር፣ ዘንድሮም በተለይ በይዞታ ማረጋገጫዎች ላይ ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር ትኩረት አድርጎ በጋራ ለመስራት ያደረገው እንቅስቃሴም መሻሻል እንዳላሳየ አንስቷል፡፡

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚቴ የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ  የሆኑት የተከበሩ ወ/ሮ አገሬ ምንአለ ባለፈው ዓመት ተቋሙ ሲስተምን ከማዘመን አኳያ የአዲስ አበባን ከተማ አስተዳደርን ለማገዝ እንደሚሰራ ቃል የገባ ቢሆንም ዘንድሮ አልተሰራም፤ በሪፖርቱ ውስጥም አልተካተተም ብለዋል፡፡

በተቋሙ አፈጻፀም በክፍተት የታዩ የውስጥ ችግሮች በደንብ ካልተገመገሙ ለማስተካከል በጣም አስቸጋሪ እንደሆኑ ጠቁመው በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ተቀምጠው ለክልሎችንም ሆነ ለሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ድጋፍ ተደርጎላቸው የተሻለ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በቋሚ ኮሚቴው የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ፉፊ ድልጋሳ በበኩላቸው አብዛኛዎቹ አፈጻፀሞች በሂደት ላይ ቢሆኑም የይዞታ ማረጋገጫ አፈጻፀም ግን በጣም ዝቅተኛና እቅዱና ሪፖርቱ ተናቦ ስላልተሰራ ተቋሙ ተልዕኮውን ከማሳካት አኳያ ችግር ላይ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አሸናፊ ጋዕሚ በኤጀንሲው ውስጥ በህጋዊ ካዳስተር የህግ ማዕቀፎች፣ በተለያዩ ስታንደርዶችና ማኑዋሎች ላይ ለ1,204 ለፌደራልና ለክልል ፈጸሚዎችና አስፈጻሚ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን፣ የካዳስተር ቅየሳ መቆጣጠሪያ ነጥብ ደህንነት ጥበቃ መመሪያ በማፅደቅ ለክልሎች መሰራጨቱን፣ የከተማ መሬት ይዞታ መብት ምዝገባና ሰርቲፊኬት የተሟላ ዝግጅት መደረጉን፣ በ8 ከተሞች ግምገማ ለማድረግና ግብረ-መልስ ለመስጠት የተቀመጠው ተግባር በእቅዱ መሰረት መከናወኑን በጥሩ አፈፃጸም አስቀምጠዋል፡፡

ዘርፈ-ብዙ ስራዎች በተመለከተ ኤጀንሲው የሴቶችን ወደ አመራርነት ከማሳደግ አንጻር ከ33% ወደ 45% ለማድረስ የተጣለው ግብ 89% መፈጸሙና የኤጀንሲውን ስራ ለህብረተሰቡ ከማስተዋወቅ አንጻር የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ተደራሽ ለማድረግ የተሰራው የልማታዊ ኮሙኒኬሽን ስራዎች 100% መድረሳቸው የተቋሙ ጠንካራ ጎኖች እንደሆኑ ገልፀ     ው በቀጣይም ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሰብሳቢው በግማሽ ዓመቱ 81,550 የመሬት ይዞታዎች የማረጋገጥ ስራ ተግባራዊ ለማድረግ ታቅዶ ለ45,114 ይዞታች የማረጋጥ ስራ በመከናወኑ አፈጻጸሙ 55.3% ዝቅተኛ መሆኑ ጠቁመው በክልል ከተሞች ወጥና ተነባቢ የሆነ የህጋዊ ካዳስተር ስርዓት ሊሸከም የሚችል የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ መዋቅር በመዘርጋትና ተቋት እንዲቋቋሙ ልዩ ትኩረት በመስጠት ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ከበደ ቋሚ ኮሚቴው በሪፖርቱ ላይ ያነሳቸውን ሀሳቦች እንደግብዓት ወስደው ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ተናግረው ከክልሎች ጋር እቅድ አውጥተውና ተፈራርመው በቅንጅት ለመስራትም ቃል ተገብቷል ብለዋል፡፡