null H.E. Prime minister Abiy Ahmed (PhD) noticed that violence and crises among the people is a major problem for the peaceful coexistence.

በህዝብ ዘንድ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር ያልተገባ እና የአገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ዴሞክራሲ አደጋ ላይ የሚጥል እንደሆነ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳሰቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ጥር 24 ቀን 2011 ዓ/ም በ5ኛ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ ልዩ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች  ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

በአገሪቱ ያለውን ወቅታዊ ሰላምና ጸጥታ በተመለከተ በመጀመሪያው ዙር ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ደክተር አብይ አህመድ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከውጭ የገቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት አስመልክቶ መንግስት ሆደ ሰፊ፣ አርቆ አሳቢ እና ችግሮችን በብስለት ካልፈታ ዴሞክራሲን በቀላሉ ለማምጣት የሚቸገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከፖለቲካ ፓርቲዎች ግማሾቹ የዴሞክራሲን መርህ ተከትለውና አክብረው ለአገራቸውና ለህዝባቸው የሚታገሉ እንዳሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሌላ በኩል ሀይልን አማራጭ አድርገው የተሰለፉና ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨትና አገሪቱን ለማተራመስ የሚሰሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በሰፊው የፖለቲካ ምህዳር ገብተው የሃሳብ ልዕልና ለማምጣት የተቸገሩ ደካማ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሉም አክለዋል፡፡

የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የግድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም የምክር ቤት አባል መሆን አይጠበቅም፣ ሁሉም ዜጋ ለሰላም የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል ሲሉም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት፡፡

ህገ-ወጥ የጦር የመሳሪያ ዝውውር እና ኮንትሮባንድ በአገሪቱ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እያደረሰ መሆኑን ገልጸው ችግሩን ለመቅረፍ ገቢዎችና ጉምሩክ ሚንስቴር የቁጥጥርና የፍተሻ አቅሙን የበለጠ ማጠናክር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩልም ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ በህግ የማይጠየቅ አካል እንዳማይኖርና የእስር ማዘዣ ወጥቶባቸው በአገር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችም በአንድ አካባቢ ተወስነው መቀመጣቸው ከስር አይተናነስም፣ ነጻ ህሊናም የላቸውም ብለዋል፡፡

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን በተመለከተም ክልል ወሰን እንጂ ሉአላዊ ድንበር እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንኛውም ዜጋ በአገር ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ የመስራትና የመኖር መብቱ ሊነፈግ እንደማይገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

በአገሪቱ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና የሚዲያ ነጻነትን በተመለከተ በሁለተኛው ዙር ከምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

ከአባላቱ ለተነሱ ጥያቄዎች ዶክተር አብይ አህመድ ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት የግብርናው ዘርፍ ማደግና መዘመን እንዳለበት እና አገሪቱ በመስኖ የማምረት አቅሟም መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በተመለከተም የህዳሴ ግድቡ በቀጣ አራት ዓመት ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅና በዚህ አመትም ከ7 የማያንሱ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ ስራ እንደሚገቡ ገልጸው በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የሚዲያ ነጻነትን በተመለከተ ከአባላት ለተነሳው ጥያቄም ዶክተር አብይ በሰጡት ምላሽ ኢትዮጵያ ውስጥ ሚዲያዎች ሚናቸውን በአግባቡ የሚወጡ እንዳሉ ሁሉ ሀላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት የሚቸገሩና አጀንዳ እየተቀረጸላቸው ህዝብን ከህዝብ እንዲያጋጩ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡

በሌላ በኩልም መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊና ተአማኒነት ባለው መልኩ ለብሄራዊ መግባባትና ለአገራዊ አንድነት መስራት እንዲችሉ ያለባቸውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ መንግስት ሁለንተናዊ ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡