null Hospital and Clinics face shortage of medicines and medical tools.

ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች የመድሃኒት አቅርቦት እና የህክምና መሳርያ ብልሽት ችግሮች እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልላዊ መንግስት ባደረገው የመስክ ምልከታ የወልዲያ፣ ላልይበላ እና የጎንደር ሆስፒታሎች እየሰጡ ያለውን አገልግሎት ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የወልዲያን ሆስፒታል በጎበኘበት ወቅት የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ጥሩ ቢሆንም በተቋሙ የደም አቅርቦት እጥረት፣ የህክምና መገልገያ ማሽኖች ብልሽት፣ የመድሂት አቅርቦት፣ የአቡላንስ እና የሰው ሀይል እጥረት እንዳለበት ተገንዝቧል፡፡

ሆስፒታሉ ገጠራማ ቦታዎችን የሚሸፍን ሲሆን በመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት እስከታች ወርዶ ለመስራት እና ነፍሰጡር እናቶችም ወደ ሆስፒታሉ መጥተው ለመውለድ ከፍተኛ ተግዳሮቶች እንዳሉባቸው የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ የህንጻ ግንባታ ጥራት ችግር እንዳለበት እና ከሚሰጠው አገልግሎት አንጻርም በቂ ክፍሎች እንደሌሉት ተጠቁሟል፡፡

በተመሳሳይም ቋሚ ኮሚቴው የላልይበላን ሆስፒታል፣ ጤና ጣቢያና ጤና ኬላ ተዘዋውሮ በጎበኘበት ወቅት የላልይበላ ሆስፒታል አገልግሎት አሰጣጡ ደረጃውን ያልጠበቀ በመሆኑ የከተማው ነዋሪዎች ቅሬታ እንዳላቸው እና ሆስፒታሉ ከሰው ሀይል ጀምሮ አስከ መድሀኒት አቅርቦት ዘርፈ-ብዙ ክፍተቶች እንዳሉበት ነው የተረዳው፡፡

የላልይበላ ጤና ጣቢያ የእናቶች ማዋለጃን ጨምሮ ከህጻናት እስከ አዋቂ ህክምና መስጫ ክፍሎች እንዳሉት እና ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን የHIV ኤድስ መድሃኒት ተጠቃሚ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም መድሀኒቱን እንዳያቋርጡ በባለሙያዎች የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ ለቋሚ ኮሚቴው ተብራርቷል፡፡

የጤና ጣቢያው በለሙያዎች እንዳሉት በላልይበላ ቅርሶች ዙሪያ የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች የመጸዳጃ ችግር እንዳለባቸው እና ቤቶቹ ተጠጋገተው የተሰሩ በመሆናቸው በየጊዜው የአተት ወረርሽኝ መነሻ በመሆን ችግሩ ሊቀረፍ እንዳልቻለ ነው የተናገሩት፡፡

በተመሳሳይም ቋሚ ኮሚቴው የጎንደርን ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና መስጫ ክፍሎችን በጎበኘበት ወቅት የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድሀኒቶች ተለይተው አለመቀመጣቸውን፣ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ተገኝተው ለተማሪዎች በስነ-ተዋልዶ፣ በኤች አይቪ ኤድስ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ ከመፍጠር አንጻር ክፍተቶች አንዳሉበት ተገንዝቧል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ጉብኝት ባደርገባቸው ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች የእናቶችን ሞት ለመቀነስ፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማዘመን የሚያደርጉትን ጥረት አድንቆ፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በየደረጃው መታገል እና በቁርጠኝነት መስራት  እንደሚያስፈልግ ለባለሙያዎች እና ለክልሉ አመራሮች አሳስቧል፡፡