null House appreciates Semera University for audit findings correction

የሰመራ ዩኒቨርስቲ በፌዴራል ዋና ኢዲተር በተረጋገጡ የኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት ማሻሻያ ማድረጉን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

በሠመራ ዩኒቨርስቲ የ2010 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ግኝት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በሰጠው የማሻሻያ ሀሳብ መስረት የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት አረጋገጠዋል፡፡

ጉብኝቱ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከግዥ ኤጀንሲ፣ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፣እንዲሁም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የመስክ የተደረገ ነው፡፡

ዩኒቨርስቲው በፋይናንስ ዘርፉ በወጪና ተስብሳቢ ሂሳቦችን በህጋዊ ደረሰኞች አስደግፎ ለመስራት ጥረት እያረገ እንደሆነ፣ በዋና ኦዲተር ምክረ- ሀሳብ መስረት ያለመመሪያ ይከፈል የነበረው የምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የትርፍ ሰዓት ክፍያ መቆሙን፣ እንዲሁም በየወሩ የባንክ ማስታረቂያ ሂሳብ እየተወራረደ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ2009 በጀት አመት የዞረ 123 ሺህ 599 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተመላሽ አለመደረጉን፣የህንድ ዜግነት ካላቸው የዩኒቨርስቲው መምህራን በወቅቱ የስራ ግብር አለመቆረጡን፣ እንዲሁም ያልተወራረዱ ወዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች መኖራቸውን አባላቱ አመላክተዋል፡፡    

በዩኒቨርስቲው የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሀብተ ወልድ ማብራሪያ ባደረጉበት ወቅት 123ሺህ 599 ብር ጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተመላሽ ያልሆነው ገንዘቡ የጠፋበት ግለሰብ በህግ ተጠይቆ መክፈል ባለመቻሉ እንደሆነ ገልጸው የህንድ መምህራን ስራ በመልቀቃቸው ምክንያት የስራ ግብር መቁረጥ እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡ ውዝፍ ተከፋይና ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለማወራረድ በሂደት ላይ እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በሰጠው ግብረ- መልስ ዩኒቨርስቲው በበጀት አጠቃቀሙ የተሻለ መሆኑን፣ የውስጥ ገቢና የመደበኛ በጀት በየወሩ በደረሰኝ እንደሚወራረድ፣ የንብረት ቆጠራው በኮምፕዩተር የተደገፈ መሆኑን በጥንካሬ ተቀብለዋል፡፡

በአንጻሩ በወጪና ተከፋይ ውዝፍ ሂሳቦች በወቅቱ አለመወራረድ፣ የካፕታል በጀት በዕቅድ አለመጠቀም፣ ከህንድ መምህራን የስራ ግብር አለመቆረጥ፣የውስጥ ኦዲት የስራ ክፍል የሰው ሀይል እጥረት እንዳለበት፣ የተማሪዎች መመገቢያና መጸዳጃ ክፍሎች የንጽህና ጉድለት የሚታይባቸው መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት በክፍተት ገምግመዋል፡፡

 

የሰመራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አደም ቦሪ በበኩላቸው በዩኒቨርስቲው ሰላም የመማር ማስተማር ቢኖርም የበጀት እጥረት በመኖሩ ምክንያት የተቋሙን መሰረተ ልማት ለማሟላት መቸገራቸውን፣ የመብራት ሀይል መቆራረጥና የውሀ አቅርቦት ማነስ በስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይም በየኒቨሲቲው የተጀመሩ ግንባታዎች ጣሪያቸው ነፋስን መቋቋም እንዲችሉ በኮንክሪት እንዲሰሩ የህንጻ ዲዛይን መደረጉን፣ ለአካል ጉዳተኞች የተሻለ ድጋፍ እንደሚደረግ፣ እንዲሁም በስርዓተ ፆታ ዙሪያ ከቤተሰብ መምሪያ ጋር በመተባበር ለተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን በጥንካራ ጎን  የተከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን ነው የቋሚ ኮሚቴው አባላት የገለጹት፡፡

በዩኒቨርስቲው የተጀመሩ የህንጻዎች ግንባታቸው እየተጓተተ መሆኑን፣ ለሴት ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ አለመሆኑን ግብረ መልሱን የሰጡት የተከበሩ አቶ ጀምበሩ ሞላ  በክፍተትነት አመላክተዋል፡፡

በመጨረሻም የተማሪዎች መመገቢያና መጸዳጃ ክፍሎች ንጽህናቸው መጠበቅ እንዳለበት የቋሚ ኮሚቴው አባላት አሳስበው ሰመራ ዩኒቨርስቲ በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱና የኦዲት ግንቶችን በማረም  ለሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አርአያ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል፡፡         

በሌላ ዜና የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ ያሉበትን የኦዲት ግንቶች ለማረም ጥረት እያደረገ እንደሆነ ተገለጸ

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ በ2010 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶችን እንዲያርም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በተሰጠው የማሻሻያ ሀሳብ ለይ የርምት እርምጃ መውሰድን ለማርጋገጥ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡

በዩኒቨርስቲው በወቅቱ ያልተሰበሰበ ገንዘብ፣ የተጋነነ የማዕቀፍ ግዥ፣ እንዲሁም ለማስታወቂያ እና ለውሀ መስመር ዝርጋታ ከፋይናንስ መመሪያ ውጭ ያላግባብ ወጪ በመደረጉ የኦዲት ጉድለቶች መከሰታቸውን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም የቋሚ ኮሚቴው አባላት የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሳይፈቅድ ለመደበኛ ስራ ገንዘብ መጠቀም፣ ከመመሪያ ውጭ ለስራ ማበረታቻ የገንዘብ ክፍያ መፈጸም፣ ከህንድ መምህራን የስራ ግብር ሳይቆረጥ የቀረ ሂሳብ እንዳለ፣ እንዲሁም ለተመራማሪዎች የስራ ማስኬጂያ ለታለመለት አላማ ስለመዋሉ ማረጋገጥ ያልተቻለ 297 ሺህ ብር እና በተከፋይ ሂሳቦች ዙሪያ የኦዲት ግኝቶች መኖራቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈቃደ ሀይለ ሚካኤል ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በወቅቱ መሰብሰብ የነበረበትን 16 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ ሳይፈቅድ ለማስታወቂያ፣ ለመደበኛ ስራ ማስኬጃ፣ ለስራ ማትጊያ፣ ይከፈል የነበረው ገንዘብ፣ አሁን ላይ በመመሪያው መሰረት የተቋረጠ መሆኑን  ነው አቶ ፈቃደ ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል አቶ ፈቃደ እንዳሉት ለጥናትና ምርምር ለዳታ ሰብሳቢዎችና ስልጠና ለሚሰጡ ባለሙያዎች የተከፈለ 297 ሺህ ብር በሰነድ የተወራረደ ቢሆንም በአንድ ሰው የተፈረመ ተመሳሳይ ፊርማ በመታየቱ ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝት ነው ማለቱን አስረድተዋል፡፡

የደብረ ብርሀን ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በበኩላቸው የኦዲት ግንቶችን ለማረም ሁለንተናዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው በሌላ በኩል የበጀት እጥረት፣ የማዕቀፍ ግዥ መጓተት እና የJEG ደረጃ ምደባ መዛባት በዩኒቨርስቲው ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አስረድተዋል፡፡

ግብረ መልሱን የሰጡት የተከበሩ አቶ ጀንበሩ ሞላ በተቋሙ የኦዲት ግንቶችን ለማረም የሚደረገውን ጥረት፣ ከቦርድ ውሳኔ ውጭ ገንዘብ ተከፋይ እንዳይሆን መደረጉን፣ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች በደረሰኝ መረጋገጣቸውን በጥንካሬ መገምገሙን አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይም የተማሪዎች መመገቢያ ክፍሎች ንጽህናቸው የተጠበቀ መሆኑን፣ደረጃውን የጠበቀ የህጻናት ማቆያ መኖሩን እንዲሁም የተማሪዎች መዝናኛ ክፍል ምቹና የተሻለ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ለመምህራን የትርፍ ሰዓት ክፍያ በልዩነት መፈጸሙን፣ ሁለት ፐርሰንት የስራ ግብር በወቅቱ ተቆርጦ ገቢ አለመሆኑን፣እንዲሁም ለምርምር ወጪ የተደረጉ የተለያዩ የአበል ክፍያዎችን ከማወራረድ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ የቋሚ ኮሚቴው አባላት ጠቁመው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በዝርዝር አስገንዝበዋል፡፡