null House criticizes Civil Service Commission for immature disclosure

በደመወዝ ስኬል ሽግግር ላይ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በቂ ግንዛቤ ባለመፍጠሩ እንደ ደመወዝ ጭማሪ ተወስዶ የመንግስት ሰራተኛ ኑሮ እንደ ከበደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ፡፡

የተደረገውን የጡረታ ጭማሪ ተጠቃሚዎች ማመስገናቸውንም ኮሚሽኑ አመለከተ፡፡

ህዳር 22 ቀን 2012 የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ከ20,000 የሚበልጡ ስራዎችን መዝኖና ደረጃ አውጥቶ ወደደመወዝ ስኬል ማሸጋገሩን ኮሚሽነሩ አቶ በዛብህ ገብረየስ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተቋሙን የሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ባቀረቡቡት ወቅት ገለፁ፡፡

ይህ የስራ ምዘናና ደረጃ ምደባ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ደረጃ ላይ ሲገኝ አዲስ በተፈጠሩ መስሪያ ቤቶች ምክንያት 1 ፔርሰንት የሚሆን ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ከኮሚሽኑ ሪፖርት ለማወቅ ተችሏል፡፡

በየተቋማቱ  በወጥነት ባለው መልክ ፕሮጀክቱ ለምን ተግባራዊ እንዳልተደረገ  እና የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ክፍያ ለምን እንደዘገየም ጠይቋል፡፡ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ የደመወዝ ጭማሪ ያለመሆኑም በቂ ግንዛቤ ለህብረተሰቡ ስላለመፈጠሩም አንስቷል፡፡

አንዳንድ ተቋማት ስራውን ዘገይተው መጀመርና ቀድሞ ስራቸውን አስመዝነው ከፍ ያለ የደመወዝ ስኬል ያገኙ ተቋማት የቀድሞን ለመከተል ፍላጎት መኖር ስራውን በሁሉም ተቋማት በተመሳሳይ ጊዜ ማጠናቀቅ እንዳልቻለ ኮሚሽነሩና የስራ ባልደረቦቻቸው አመልክተዋል፡፡

ስለደመወዝ ስኬል ክፍያ መዘገየትም ሲመልሱ፤ ስራዎችን የማስመዘንና ደረጃ የማውጣት ሂደት አዲስ በተፈጠሩ መስሪያ ቤቶች ምክንያት 1 በመቶ ስራ በኮሚሽኑ እጅ መኖር፣ በተመዘነው ስራ ላይ ሰው መመደብ በኩል በሁሉም ተቋማት ስራው ቢጠናቀቅም 5 ተቋማት መኖራቸው፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል ከአደረጃጀት ለውጥ ጋር በመጡ ልዩነቶች በእያንዳንዱ 1,200 የሚደርሱ የስራ መደቦች የኮሚሽኑን ማረጋገጫ ያለማግኘታቸው እንደሆኑ ሃላፊዎች አስረድተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስራ በጥቅምት ወር ያለቀ ሲሆን የኦሮሚያው እየተሰራ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በአዲስ ስኬል መሰረት ክፍያ መፈፀምን እንዳጓተቱ የኮሚሽኑ የስራ ሃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡

በተመዘነው ስራና ደረጃ በወጣለት መደብ ላይ ሰራተኛ ተመድቦ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ክፍያ እንደተጀመረ ተደርጎ በመንግስት በኩል በመነገሩ ህብረተሰቡ መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ጨምሯል በሚል እሳቤ ሁሉም ነገር ላይ ዋጋ ተጨምሮ መንግስት ሰራተኛው ምንም ነገር ሳያገኝ ለተጨማሪ ወጪ መዳረጉን ኮሚቴ አንስቷል፡፡ መንግስት ሰራተኛው ለዚህ ጉዳት የበቃው የደመወዝ ስኬል ማሻሻል ማለት የደመወዝ ጭማሪ ያለመሆኑን ኮሚሽኑ ተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ባለማስጨበጡ የመጣ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ በሚዲያ ጉዳዩን ለማሳወቅ ሞክራለሁ የሚል መከራከሪያ ነጥብ ቢያነሳም ቋሚ ኮሚቴው ተከታታይነት ያለው ስራ ኮሚሽኑ ይጠበቅበት ነበረ አቋም አራምዷል፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ኮሚሽኑ ከመንግስት በቀረበለት ጥያቄ የጡረታ ክፍያ ፓኬጅ በአጭር ጊዜ ሰርቶ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለጡረተኛ የመንግስት ሰራተኞች የክፍያ ጭማሪ ማድረጉንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ በዚህ መሰረትም ዝቅተኛው የክፍያ መጠን ከብር 700.00 ወደብር 1258 ማደጉ ተመልክቷል፡፡

ተጠቃሚዎችም እነሱ ባላሰቡትና መንግስትም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ይህን የመሰለ እርምጃ በመውሰዱ መደሰታቸውንም ከሪፖርቱ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ከጡረተኞች ከ80 በመቶ በላይ ከድህነት ወለል በታች ገቢያቸው እንደሆነ ያመለከተው ሪፖርቱ የጡረታ ፈንዱ አስተዳደር ችግር ያለበት በመሆኑ ገንዘቡን አትራፊ በሆነ ስራ ላይ አውሎ ጡረተኞችን መደገፍ እንዳልተቻለ ያወሳው ሪፖርቱ የመንግስት ግምጃ ቤት ጨረታም አዋጂ ያለመሆኑ ተመልክቷል፡፡ ስለዚህ ተቋሙ የአደራ ገንዘቡን በነፃነት ማንቀሳሰቅ የሚችልበት የህግ ድጋፍ እንዲኖረው ኮሚሽኑ የምክር ቤቱን ድጋፍ ጠይቋል፡፡

የስብሰባውን መድረክ የመሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወይዘሮ እምዬ ቢተው ኮሚሽኑ ሰራተኛውን በዕቅዱ ላይ ጥሩ ግንዛቤ ፈጥሮ ወደስራ እንዲገቡ ማድረጉ ጥሩ መሆኑን ጠቁመው በተለይ የደመወዝ ስኬል ማሻሻያ የመንግስት ደመወዝ ጭማሪ ተደርጎ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሳውን የተሳሳተ አረዳድ ለማስተካከል ኮሚሽኑ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እንዲፈጥር አሳስበዋል፡፡   

ዘጋቢ:- ናምሲ አልቃ