null House discusses, redirects three bills

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

ታህሳስ 7-2012 . የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6 መደበኛ ስብሰባው ሶስት የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያየቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል፡፡

የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ሲሆን አዋጁን አስመልክቶ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስተር ዴኤታ የተከበሩ አቶ ጫላ ለሚ ማበራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የአዋጁ አላማ የስራ ዕድል ፈጠራ፣የቴክኖሎጂ፣ ዕውቀትና ክህሎት ሽግግርን እንዲሁም የውጪ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ እና የሃገሪቱን የተፈጥሮ ሃብቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት መሰረታዊ ምክንያት የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት በማፋጠን የእድገቱን ዘላቂነት ማረጋገጥ፣ የሃገር ውስጥ የማምረት አቅምን ማጠናከር እንዲሁም የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

በዚህ አዋጅ ዙሪያ ከምክር ቤቱ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል ኢንቨስትመንቱን ለመጀመር የሚሰጠው የሁለት አመት የጊዜ ገደብ ተገቢ እንዳልሆነና ከዛ ያነሰ ጊዜ መሆን እንዳለበት እንዲሁም ሌሎችም ሊታዩ የሚገባቸው ጉዳዮችን ተነስተዋል፡፡ አዋጁ ረቂቅ አዋጅ ቁጥ16/2011 ሆኖ በዋናነት ለንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና በተባባሪነት ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

በተጨማሪም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ስለ ማዛወር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል፡፡

በውይይቱ ከምክር ቤቱ አንዳንድ የልማት ድርጅቶች ከግል ይልቅ በመንግስት ቢያዙ የተሻለ የሚሆኑ እንዳሉና ድርጅቶቹ ወደ ግል በመዛወራቸው የሚያመጡት ጥቅምና ጉዳት ተገቢው ጥናት መደረግ እንዳለበት ተነስቷል፡፡ በተጨማሪም በሙሉ በከፊል የሚዛወሩት ድርጀቶች ተለይተው መቀመጥ አንዳለባቸው ተገልጿል፡፡ አዋጁ አዋጅ ቁጥር 17/2012 ሆኖ ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሶሰት ተቃውሞ በስድሰት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ለዝርዘር እይታ ተመርቷል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ተወያይቷል፡፡ በውይየቱም ከህብረተሰብ ጤና አኳያ ትንባሆ ላይ የተጣለው ታክስ ዝቀተኛ ስለሆነ የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ቢያየው የሚልና ሌሎችም መታየት ያለባቸው ሃሳቦች ቀርበዋል፡፡ አዋጁም ረቂቅ አዋጅ ቁጥር18/2012 ሆኖ ለገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ በሙሉ ድምጽ ተመርቷል፡፡

ዘጋቢ:-ፋንታዬ ጌታቸው