null House endorses two bills

ምክር-ቤቱ ሁለት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 7ኛ መደበኛ ስብሰባው በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል የተፈጥሮ ጋዝ ለማስተላለፍ በሚረዳ የቧምቧ መስመር ዝርጋታ እና የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ፡፡

የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲሃ የሱፍ በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል የተፈጥሮ ጋዝ የቧምቧ መስመር ለማስተላለፍ የተደረገውን ስምምነት ለማጽደቅ የወጣውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክተው ለምክር ቤቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውም ረቂቅ አዋጁ ከአስረጅዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ሰፊ ውይይት ሲደረግበት መቆየቱን አስታውሰው በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ስምምነት ዓለም አቀፍ የስምምነት ደረጃን መስፈርት የሚያሟላና ሁለቱ አገራት ሊተገብሯቸው የሚገቡ ተግባራትን በዝርዝር ያስቀመጠ አዋጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አዋጁ ስምምነቱን በመፈጸም ሂደት ችግሮች ቢፈጠሩ በሁለቱ አገራት መካከል ሊደረጉ የሚገቡ ድርድሮችን እና ይህ ሳይሆን ቢቀር በዓለም አቀፉ የዳኝነት ሂደት እንደሚታይ በግልጽ መደንገጉን እንዲሁም አገራችን ለረጅም አመታት ባላት የተፈጥሮ ጋዝ ለመጠቀም እያደረገች ያለውን ጥረት ተግባራዊ የሚያደርግ ስምምነት መሆኑንም ወ/ሮ ፈቲሃ የሱፍ አክለው አብራርተዋል፡፡

የህግ፤ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ አበበ ጎዴቦ በበኩላቸው የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ቋሚ ኮሚቴው ከባለድርሻ አካላትና ከአስረጅዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማካሄዱንና በማቋቋሚያ አዋጁ ውስጥ በርካታ ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱም ሂደት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አገሪቱ በፊርማ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች መሰረት እስረኞችን በማረምና በማነጽ የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት የሚያስችል መሆኑ፣ የተቋሙን አደረጃጀት የተሻለ በማድረግ እስረኞች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው ከጥፋታቸው ታርመው እንዲወጡ በማድረግ ሰላማዊ ህይወት እንዲኖሩ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑ የሚሉት በጭብጥነት መለየታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

አዋጁ ነፍሰ ጡር ሆነው ገብተው በማረሚያ ቤት ቆይታቸው የሚወልዱ እና ህጻናት ይዘው የሚገቡ እናቶች ተመጣጣኝ ምግብና ልዩ እንክብካቤ የሚያገኙበትን፣ የአካል ጉዳተኞች ታራሚዎች አያያዝ የሚሻሻልበትንና መገናኛ ብዙሃን ስለእስረኞች አያያዝ በማረሚያ ቤት ተገኝተው መጎብኘት የሚችሉበትን ሁኔታ የሚደነግግ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል አቶ አበበ፡፡

አቶ አበበ አክለውም ረቂቅ አዋጁ በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች ሰብአዊ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ታርመው፣ ታንጸውና አምራች ዜጋ ሆነው ከማረሚያ ቤት ሲወጡ ለራሳቸውና ለአገራቸው የሚጠቅሙ ሆነው ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል እንዲሁም ባላቸው ሙያ ተደራጅተው መስራት የሚያስችላቸው መሆኑንም በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል፡፡

ምክር ቤቱም ለታራሚዎች ስለሚጥ ምህረት፣ ከእስር ለተፈቱ ታራሚዎች ስለሚደረግ ክትትልና ድጋፍ እና የአመክሮ አሰጣጥ ሁኔታዎች ላይ የማብራሪያ ጥያቄዎችን አንስቶ ከተብራሩለት በኋላ የቀረቡለትን ሁለት ረቂቅ አዋጆች መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ዘጋቢ:- ድረስ ገብሬ