null House reminds Large Tax-payers Office focus on liabilities

የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በውዝፍ እዳ አሰባሰብ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው አስገነዘበ፣

አዲስ አበባ ህዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም.፤በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን የ4 ወራት እቅድ አፈጻጸም በአካል ተንቀሳቅሶ ተመልክቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ አመራሮችና ሰራተኞች እንዲሁም ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋርም በተቋሙ አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ተሬሳ እንሴሱ የ4 ወራት እቅድ አፈጻጸማቸውን አስመልክተው እንደተናገሩት ተቋሙ የታክስና የሽያጭ መረጃ ለመሰብሰብ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሆነና ነገር ግን የቴክኖሎጅ መሰረተ ልማቱ መቋራረጥ በተፈለገው ደረጃ እንዳንሄድ እንቅፋት እንደሆነበት አስረድተዋል፡፡

የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን አጠቃቀም ላይ ያለውን የአመለካከት ችግር በስልጠና ለማስተካከል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን በአካል በመንቀሳቀስ ጭምር ተግባራዊ መደረጉን የማረጋገጥ ስራም እንሰራለን ያሉት ሥራ-አስኪያጁ ነገር በቢሮ ተቀምጠን የምንቆጣጠርበት ቴክኖሎጅ ቢኖር ስራችንን ስኬታማ ያደርገዋል በማለት ተናግረዋል፡፡

ግብራቸውን በወቅቱ በማሳወቅ የሚከፍሉ አገር ወዳድ ዜጎች የመኖራቸውን ያህል በወቅቱ የማያሳውቁና ታክስ በመሰወር አገሪቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርጉ ግብር ከፋዮችም እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ተሬሳ ይህን ችግር ለመፍታት ሚቻለው ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ስለሆነ ይህንኑ ተግባራዊ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

በውዝፍ እዳ አሰባሰብ ረገድ እስካሁን ከላው አጠቃላይ 42 ቢሊዮን የሚጠጋ ውዝፍ ተሰብሳቢ እዳ ውስጥ በ4 ወሩ ለመሰብሰብ ከታቀደው 6 ቢሊዮን ብር ገደማ ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የእቅዱን 65 በመቶ ማሳካት እንደቻሉ የገለጹት ሥራ-አስኪያጁ ከአጠቃላይ እዳው አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ አፈጻጸም በመሆኑ በበጀት አመቱ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ትኩረት ስጥተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ከፍተኛ ግብር ከፋዮች በበኩላቸው የተጭበረበረ ደረሰኝ መጠቀምን አስመልክተው እንዳሉት እኛ ደረሰኝ እንጠቀማለን እንጅ አናትምም በመሆኑም መንግስት ህገ-ወጥ ደረሰኝ በሚያትሙት ላይ ህጋዊ እርምጃ ሊወስድ ይገባል እንጅ  እኛን ማሳደድና አላሰራ ማለት የለበትም ብለዋል፡፡

የታክስና ግብር ህጉ ግዴታ የሚጥለው በግብር ከፋዩ ላይ ብቻ ሳይሆን በአስከፋዩም ላይ ሊሆን እንደሚገባ በአጽንኦት የተናገሩት ግብር ከፋዮቹ ፍትሃዊ ያልሆነ ግብርና ታክስ መጣል ግብር ከፋዩን ብቻ ሳይሆን አገሪቱንም ሊጎዳ እንደሚችል ተገንዝቦ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚጣለውን ግብርና ታክስ ለመወሰን እንዲሁም ኦዲት ለማድረግ ዘርፉን በጥልቀት ማወቅ ስለሚጠይቅ መንግስት ሊያስብበት ይገባል ብለዋል፡፡

ግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ ትኩረት ማድረግ ያለበት ከፍተኛ ግብር መሰብሰብ ላይ ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ግብር ማስከፈል ላይ መሆን አለበት ያሉት ግብር ከፋዮቹ ፍትሃዊነት በጎደለው ግምት ምክንያት በአገራችን ሰርተን ለመኖር ተቸግረናል ብለዋል፡፡

ከውጭ ወደ አገር ውስጥ እቃ ስናስገባ ጉምሩክ ላይ ባለው ህገ-ወጥ የፍተሻ ስርዓት እቃችን እተጉላላና ከጥቅም ውጭ እየሆነ ስለሆነ ጉምሩ የፍተሻ ስርዓቱን ሊያዘምንና የሰራተኞቹንም ስነ-ምግባር ሊፈትሽ ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በግብር ማሳወቅና አሰባሰብ እንዲሁም የውዝፍ እዳ መረጃን በመለየት ረገድ የሰራው ስራ በጥንካሬ የሚወሰድ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብሏል፡፡

ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በፌደራል ዋና ኦዲተር ከተረጋገጠው 42 ቢሊዮን ብር ውዝፍ እዳ ውስጥ እስካሁን መሰብሰብ የቻለው 4 ቢሊዮን ብር ገደማ በመሆኑ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳለው ማሳየት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ነው ሲልም ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

የታክስ አወሳሰንና አከፋፈል ላይ ያጋጠመው ችግር የግንዛቤ ስራውን በቂ አለመሆን የሚያመላክት በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ያለው ቋሚ ኮሚቴው የህግ ማስከበርና የገልግሎት አሰጣጥ ስራውን ማቀላጠፍም ትኩረት የሚፈልግ ነው ብሏል፡፡

ኮንስትራክሽን ዘርፉን በትክክል አውቆ ኦዲት የማድረግ ክፍተት አለ የተባለውንና ሌሎችም በግብር ከፋዮች የተነሱ ቅሬታዎችን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ እንዲሁም ግብር ከፋዮች ተቀራርበው በመነጋገር ችግሩን በዘላቂነት መፍታት ይጠበቅባቸዋል በማለት አሳስቧል፡፡  

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በበኩላቸው የተሰጠውን አስተያየት ተቀብለው ለማስተካከል እንደሚሰሩ አስታውሰው ነገር ግን ደንብ የሚወጣው አዋጅ ከወጣና ወደ ስራ ከገባ በኋላ ስለሆነ የአሰራር ክፍተት ስለሚፈጥር ቋሚ ኮሚቴው ሊያግዘን ይገባል ብለዋል፡፡

ዘጋቢ:- ድረስ ገብሬ