null Immigrant Affairs Draft bill should be scrutinized before endorsing

የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጁ ከመጽደቁ በፊት በጥልቀት ሊታይና የአገሪቱን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ሊሻሻል ይገባል ሲል በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፣

ቋሚ ኮሚቴው ከውጭ ግብኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በጋረ በተመራላቸው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡

ስደተኞች በአገሪቱ ላይ ስለሚኖራቸው የማህበራዊ አገልግሎት ጫና፣ ስለሚፈጥሩት ሃብትና ለዜጎቻችን በምንፈጥረው የስራ እድል ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተጽዕኖ የተመለከቱ ጥያቄዎች በውይይቱ ተነስተዋል፡፡

የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ ጉዳዮች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ጫኔ በረቂቅ አዋጁ መነሻ ሃሳብና ከተሳታፊዎች በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በማብራሪያቸውምአገራችን ያካባተችው ስደተኛን የመቀበል ታሪክ፣ የተቀበልናቸው አለም አቀፍ ስምምነቶችና አሁን ያለንበት የለውጥ ሂደት ህጉን ለማሻሻል እንደመነሻ መወሰዳቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አንስተው ለስደተኞች የተሻለ ከለላ የሚሰጥና ለችግሮቻቸው ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኝ በአለም አቀፍ መመዘኛዎች መሰረት የተቀረጸ የተሟላ የህግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ በስራ ላይ ያሉ ህጎች ተግባራዊ በሚደረጉበት ጊዜ ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት ህጉን ማሻሻል አስፈልጓል ብለዋል፡፡

አገራችን ስደተኞችን ተቀብላ በማስጠለል በኩል ረጅም ታሪክ ያላት ቢሆንም ህጉ የተሟላ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ በኩል ክፍተት በመኖሩ ምክንያት ስደተኞች በአገራችን እየተረዱ ከመቀበጥ ውጭ በልማት የሚሳተፉበትና ንብረት የሚያፈሩበት እድል ተነፍጓቸው ቆይተዋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሉ አቶ ከበደ ስደተኞች ጥገኝነት ባገኙበት አገር ከዜጎች እኩል የትምህርትና የስራ እድል የማግኘት እንዲሁም ተደራጅተው የመስራት መብታቸው እንዲከበር ማድረግ የአገርን ገጽታ ከመገንባቱም ባሻገር ከአጎራባችም ይሁን ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር የሚኖረውን የወዳጅነት ግንኙነት ስለሚያጠናክር አገራችንም በተለያየ ጊዜያት የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ ስምምነቶች በመመርመርና ከራሳችን ሁኔታ ጋር በማጣጣም ህጉን ማሻሻል ያስፈልጋታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ስደተኞች ጥገኝነት ባገኙበት በአገራችን ለሚያገኙት ማንኛውም አገልግሎት ወጪው የሚሸፈነው ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገኝ ብድርና እርዳታ ስለሆነ በአገራችን ላይ ምንም አይነት የበጀት ጫና አይኖረውም ያሉት አቶ ከበደ ጫኔ ለስደተኞች ተብሎ በሚፈጠረው የስራ እድልም የአገራችን ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑና ስደተኞቹም በሚያገኙት አገልግሎት እንደማንኛው የአገሪቱ ዜጋ ታክስ እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል፡፡

 

ስደተኛን አለመቀበል ከአለም አቀፍ ስምምነቱ አኳያ አስቸጋሪ ከመሆኑም ባሻገር ገጽታም ስሚያበላሽ ስደተኞችን ተቀብለን በእርዳታ ብቻ ከምናስቀምጥና የተፈጥሮ ሃብታችንን ከምንጎዳ በልማቱም እንዲሳተፉ ብናደርጋቸው ለአገራችን የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ ነው ብለዋል አቶ ከበደ ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው አዋጁ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም የተሟላ ባለመሆኑ የአገራችንንና የዜጎቻችንን መብትና ጥቅም በማይጎዳ መልኩ እዲሻሻል መደረጉን በጥንካሬ አንስተው አሁንም ህጉ ከመጽደቁ በፊት መታየት ያለባቸው ነገሮች በጥልቀት እንዲታዩና ስደተኞችን መቀበል ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን ድረስ የደረሰብንን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ሊፈታ የሚችል ህግ ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡