null Inquiry Board inspect #COVID-19 solidarity response fund

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ ከበጎ አድራጊዎች የተሰባሰበ ንብረቶችን ጎበኘ፣

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳደርስ እያደረገ ያለው ቅድመ ዝግጅት የሚበረታታ መሆኑ ተገለጸ፣ አስተዳደሩ  ከበጎ አድራጊዎች ያሰባሰባቸው ንብረቶችም ተጎብኝተዋል፡፡

ሚያዚያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ የከተማው አስተዳደር የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከልና ወረርሽኑ የከፋ ጉዳት እያደረሰ ቢመጣ በተለይ ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችን ለመደገፍ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያሰባሰባቸውን ንብረቶች ብሄራዊ ኤግዚቢሽን ማዕከል በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

የወጣቶችና የበጎ ፍቃደኞች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ብርሃም ታደሰ በከተማዋ ቫይረሱ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በማህበራት የተደራጁና በግለሰብ ደረጃ 3,884 ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ስራ መሰማራታቸውን አብራርተዋል፡፡

የበጎ ፍቃድ አድራጊ ወጣቶች ገንዘብን ጨምሮ ሀብት የማሰባሰብ፣ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የመስጠትና እጅ የማስታጠብ፣ ደም የመለገስ እንዲሁም የተሰበሰበውን ሀብት በነጻ ከመኪና የማውረድ፣ የመጫን እና በመጋዘኖች የመደርደር ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ኃላፊው በመጋዘኑ ከተከማቹ ንብረቶች ውስጥ ያልተፈጨ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ፍርኖ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ፍራሽና ብርድ ልብሶች፣ ፓስታና ማካሮኒ፣ የንፅህና መጠበቂዎች በዋነኛነት እንደሚገኙበት ገልፀዋል፡፡ ንብረቶቹ እንዳይበላሹ በአይነት በአይነት ተለይተው መቀመጣቸውንም ተናግረዋል፡፡

በኤግዚቢሽን ማዕከል ተገኝተው ክምችቱን የተመለከቱት የቦርዱ አባላት ከበጎ አድራጊዎች የተለገሱትን የምግብና ንፅህና መጠበቂ ቁሳቁስችን ከመኪና ላይ ተሸክሞ በማወረድና ወደመጋዘኑ በማስገባት ለበጎ አድራጊ ወጣቶች አለኝታነታቸውን አሳይተዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት እና የቦርዱ አባላት የቫይረሱ ወረርሽኝ በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ የከተማ አስተዳደሩ ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አድንቀዋል፡፡

ገንዘብን ጨምሮ ከበጎ ፍቃደኞች የተሰበሰቡት ሀብቶች ለብክነት እንዳይጋለጡ እና ክፍፍሉም ከአድሎ የፀዳ እንዲሆን ተገቢውን ክትትል ማድረግ እንዲሁም የሀብቱ አሰባሰብ ህጋዊ በሆነ መንገድ ብቻ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡      

ዘጋቢ:- ኃ/ሚካኤል አረጋþኝ