null Inquiry Board observed detainees

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ አዋጁን በመተላለፋቸው ሳቢያ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ተዟዙሮ ተመልክቷል፡፡

ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም (ዜና ፓርላማ) ቦርዱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን በመተላለፋቸው ምክንያት በ3 ት/ቤቶች ውስጥ በቁጥጥር ስር ውለው የቅጣት ውሳኔያ በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ግለሰቦችን በአካል በመገኘት ተመልክቷል፡፡

በአያያዛቸው ዙሪያም ከፖሊስ አመራሮችና በቁጥጥር ስር ከዋሉ ግለሰቦች ጋርም ተወያይቷል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት የመስክ ምልከታውን ዓላማ ካስተዋወቁ በኋላ የክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር ስለዋሉ ሰዎች ሰብኣዊ አያያዝ እና የፍርድ ሂደት ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አድማሱ ኡፋ አዋጁን በመተላለፍ እና ለኮሮና ቫይረስ አጋላጭ በሆነ ሁኔታ በርካታ ሰዎችን ሰብስበው ሺሻ ሲያስጨሱ፣ ጫት ሲያስቅሙና መጠጥ ሲሸጡ የተገኙ 48 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 8ቱ ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

32ቱ በፍድር ቤት የቅጣት ውሳኔ አግኝተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንና ቀሪዎቹ የፍርድ ቤት ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

ፖሊስ ከ874 በላይ መታሰር የሚገባቸውን ሰዎች ቢይዝም ቀድሞ ማተማር ተገቢ ነው በሚል በማስተማርና ምክር በመስጠት መልቀቁንም ጠቁመዋል፡፡ የተያዙ ሰዎችም በአንድ ክፍል 4 ሆነው ተራርቀው እንዲቀመጡ መደረጉንና በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት በየጊዜው ሙቀታቸው እንዲለካ እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

አዋጁን የተላለፉ ሰዎች በመደበኛው ማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ከማድረግ ይልቅ ት/ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ለብቻቸው ተለይተው ጉዳያቸው እንዲታይ ማድረጉ ተገቢ በመሆኑ በት/ቤቶች እንዲቆዩ መደረጉም ተገልጿል፡፡       

 

ለፖሊስ አባላቱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክን ጨምሮ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አየቀረቡ ቢሆንም እጥረት እንዳለም አክለዋል፡፡

ተከሳሾች በበኩላቸው በአዋጁ ላይ የተከለከሉትን ድርጊቶች መፈጸማቸውን ቢያምኑም ፍ/ቤት በቶሎ እንደማይቀርቡ ለቦርዱ አባላት አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይም ቦርዱ በአርበኞች አፀደ ህጻናት ት/ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ በቁጥጥር ስር የዋሉ 6 ግለሰቦችን የተመለከተ ሲሆን ግለሰቦቹ ብዙ ሆነው ጫት ሲቅሙና ካርታ ሲጫወቱ መያዛቸውን የወንጀል ምርመራ ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑት ኢንስፔክተር ብርሀኑ ቤኛ ለቦርዱ አባላት አብራርተዋል፡፡

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ በአዋጁ ላይ የተቀመጡትን ክልከላዎች የተላለፉ 356 ሰዎች ከሺሻ፣ ከመጠጥ፣ ከጫት እና ከቁማር ቤቶች መያዛቸውንና 15ቱ ለምርመራ ቀርበው ከእነዚህ ውስጥ 9ኙ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶባቸው ከ500 እስከ 9‚000ብር ተቀጥተው መለቀቃቸውን 6ቱን ደግሞ ፍርድ ቤት ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ ሌሌቹ በምክርና በማስጠንቀቂ መለቀቃቸውን አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈፃጸም መርማሪ ቦርድ አባላት በምስራቅ ጎህ አንደኛና መለስተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በመገኘት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተከለከሉትን ድርጊቶች ፈፅመው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን ተመልክተዋል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጴጥሮስ ወ/ሰንበት በመስክ ምልከታው ማጠቃለያ በሰጡት አስተያየት በሶስቱም ት/ቤቶች ውስጥ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የተቀመጡ ክልከላዎችን በመተላለፋቸው ምክንያት በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ላይ ያለው የሰብአዊ አያያዝ፣ ርቀትን የጠበቀ መኝታ ክፍልና የምግብ አቅርቦትን በጠንካራ ጎን አንስተዋል፡፡

በሌላ በኩል በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦችን በፍጥነት ወደ ፍርድ አቅርቦ የቅጣት ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ አሁንም ውስንነት እንደሚታይ ገልጸው በቀጣይ መታረም እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የጸጥታ የአካላት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆኑ እያከናወኑ ያለው ተግባራት የሚበረታታ መሆኑንም ጠቁመው፤ ቅድመ የማስተማር ስራዎችም በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል ሲባል መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢያውጅም አዲስ አበባን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አዋጁን በመጣስ በርካታ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን ጠቁመው በመንግስት በሆደ ሰፊነት በምክርና በማስተማር ቢለቅም አሁንም ቸልተኝነት እንደሚታይ ጠቁመው ማህበረሰቡ ይህንን በመገንዘብ ተገቢውን ጥኝቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ነው ያገነዘቡት፡፡      

ዘጋቢ፡- ኃ/ሚካኤል አረጋኸኝ