null Melkasa-Methara, Abomsa-Dibu road projects face delay

ከመልካሳ - መተሀራ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት ባለድርሻ አካላት ቅንጅት ፈጥረው ባለመስራታቸው ኘሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት ሆኗል ተባለ፡፡

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና አርሲ ዞን የሚገኘውን መልካሳ- ሶደሬ-ኑራሄራ-መተሀራ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡

ሁለቱን ዞኖችን የሚያገናኘው ዘጠና አራት ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገድ ፕሮጀክት አምስት ወረዳዎችን የሚያካልል ሲሆን  1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በ2010 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ሥራው መጀመሩን የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሐንዲስ ሲሳይ ጃገማ ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው አገር በቀል በሆነው የንኮማድ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሚሰራው ይህ የመንገድ ስራ ለሶስት ዓመት ኮንትራት ውል ተፈጽሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውሶ   እስካሁን በዕቅዱ መሰረት 55 ኪሎ ሜትር መድረስ ሲገባው 12 ኪሎሜትር ብቻ መሆኑ ከፍተኛ የአፈጻጸም ክፍተት በመኖሩ በድክመት ገምግሟል፡፡

የፕሮጀክቱ አማካሪ የሆኑ አቶ ፋልማታ አቶምሳ ፕሮጀክቱ ሁለት የስራ ዓመታት የተጓተተ ጊዜ እንዲያሳልፍ በይዞታ ችግር እንዲሁም 772 የሚሆኑ የመብራት ምሶሶዎች  ባለመነሳታቸው 50 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የሥራው አካል  ለተቋራጩ ተላልፎ ባለመሰጠቱ የተከሰተ እንደሆነ ገልፀው ቀሪውን ሥራ አለመስራት የስራ ለመስራት በተቋራጩ በኩል ተነሳሽነቱ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

ከወሰን ማስከበር ጋርም የነጠላ ዋጋ ተመን ከወረዳ ወረዳ ልዩነት በማሳየቱ ለክፍያ መቸገራቸው እና ተመን የወጣላቸውን ክፍያውን ፈጽሞ ቦታውን ለስራ ክፍት አለማድረግ እንዲሁም ተከፍሎ ነጻ ያልኆኑ የመንገድ ክፍሎችም መኖራቸውን ነው አማካሪው ያብራራው፡፡

የፕሮጀክቱ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ይትባረክ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የሚሰራበት አከባቢ  በመስኖ ልማት ከፍተኛ ምርት የሚሰጥና የኢንቨስትመንት መሬት ያለበት መሆኑ ካሳ ክፍያ ያላለቀ በመሆኑ በተቆራረጠ ሁኔታ ለመስራት መገደዳቸውን እና ለመስሪያ የሚሆን ተስማሚ የአፈር ቦታ የማግኘቱም ሂደት ዘግይቶ መሰጠቱ ስራውን እንዳስተጓጎለ ነው የተናገሩት፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ተቋራጩ ውል በገባው መሰረት መንገዱን በወቅቱ ለማጠናቀቅ በሚያስችል አቋም ላይ ለመድረስ በቂ የሰው ሃይል እና ቁሳቁሱ በማሟላት በሙሉ አቅሙን ተጠቅሞ እየሰራ እንዳልሆነ በምልከታው ወቅቱ  ቋሚ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

መንገዱ ከፍተኛ የህብረተሰብ ሮሮ ያለበት መሆኑን ያነሱት የወረዳ አስተዳደሮች ስራው ቶሎ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ የመሬትና የንብረት ካሳ ጉዳይ ጊዜ ሳይሰጥ ተጠናቆ ወደ ስራ የሚገባበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያደረጉት ሂደት ቀጣይና አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ፕሮጀክቱ በሁሉም ባለድርሻ አካላት አማካሪ፣ ተቋራጭና  ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣንን ጨምሮ የቅንጅት ማነስ ለስራው መጓተት ዋና ምክንያት በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ የሚያሰራቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ታቅዶ በመሆኑ  በልዩ ትኩረት እንደሰራ የቋሚ ኮሚቴው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡

በሌላ ዜና የተቋራጩ የውስጥ አቅም ማነስ ለፕሮጀክቶች አፈጻጸም ማነስ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ተባለ፡፡

የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና የትራንስፖር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦሮሚያ ክልል እየተሰራ ያለውን አቦምሳ- አሴኮ- ዲቡ ወንዝ ድረስ የሚሰራውን የመንገድ ፕሮጀክት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በሚፈለገው መጠን እየተሰራ መሆኑን በአካል ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በጉብኝት ወቅት ከስራው ተቋረጭ፣ ከአማካሪ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  እና ከወረዳው አመራር አካላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በስራው ላይ የሚታዩትን ጠንካራ ደካማ ጎኖችን ለይቶ በማውጣት ጠንካራ ጎኖች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ለማስቻል በትኩረት እየተሠራ  ነው፡፡

የመንገዱን ስራ በውል ከመንግስት የተረከበው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ሲሆን የፕሮጀክቱ የግንባታ ዓይነት ከጠጠር ወደ አስፋልት ማሳደግ እንደሆነና አጠቃላይ ርዝመቱ 60 ኪሎ ሜትር መሆኑን የተናገሩት የተቋራጩ ዋና መሐንዲስ አቶ ዳዊት ወልዴ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በዕቅዱ መሰረት በሁለት ዓመታት ከ60 ኪሎ ሜትር በላይ ተሰርቶ መድረስ ሲገባው 20 ኪሎ ሜትር ብቻ መሰራቱ አፈጻጸሙን 44 በመቶ ዝቅ ማድረጉን ጠቁመው አልፎ አልፎ  የሚነሳው የወሰን ማስከበር፣ ለስራ የሚውሉ ማሽነሪዎች ዕጥረትና መንገዱ የሚሰራበት አከባቢ አመቺ ካለመሆን ባሻገር የተቋራጩ የውስጥ የበጀት አቅም ለተግዳሮቱ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ ነው አቶ ዳዊት ያብራሩት፡፡

አቶ ዳዊት በምልከታው ወቅትም የስራ ተቋራጩ ለስራው ያለው ተነሳሽነት ማነስ እንዳለ ሆኖ ለስራው የሚውሉ ማሽነሪዎች በመንገዶች ባለስልጣን በወቅቱ አለማቅረቡን ቢያነሳም በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በኩል ተቋራጩ የሚያስፈልጉ ማሽነሪዎችን እንዲገዛ ብድር ተመቻችቶለትም ግዥ ባለመፈጸሙ ብሩን ተመላሽ እንዲያደርግ የማድረግ ሂደት ላይ መድረሱን ቋሚ ኮሚቴ በድክመት ገምግሟል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መሐንዲስ የሆኑት አቶ ቀናው መሐሩ የፕሮጀክቱ ግንባታ በኮንትራት ውሉ መሰረት በተያዘለት ጊዜና ወጪ ጥራቱን ጠብቆ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲደርስ የክትትልና ቁጥጥር አግባብ በእውቀት ላይ ተመስርቶ ለመምራትና አፋጣኝ መፍትሔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን ለይተው በመስራት ባለመቻሉ ተቋራጩ በሙሉ አቅም እንዲሰራ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉን አብራርተዋል፡፡

የአስኮ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገቢ ጉልቻ የአከባቢው ህብረተሰብ ለአስራ አንድ ዓመታት ሲጠይቅ የኖረው ጉዳይ በመሆኑ  ህዝቡ መንገዱ ተጠናቆ ለማየት ካለው ጉጉት የተነሳ ካሳ ሳይከፈል መንገዱን ለስራ ነጻ ማድረጉ ከምንም በላይ ሊበረታታ የሚገባ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ጠቁሟል፡፡

አቶ ገቢ አክለውም ፕሮጀክቱ በሶስት ዓመታት ተሰርቶ እዲጠናቀቅ የታቀደ ቢሆንም አሁን ባሉት አስር ማሽነሪዎች እና እየታየ ባለው የስራ እንቅስቃሴ የሚቀጥል ከሆነ የአከባቢውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ማረጋጥ ቀርቶ የህዝቡ ሮሮው የከፋ እደሚሆን ለቋሚ ኮሚቴው አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ በማድረግ መንገዱ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት  እንዲውል በተለይ ተቋራጩ  ሥራውን የሚመጥን ተጨማሪ ማሽኖችንና የሰው ሃይል በማሟላት በወቅቱ ለማጠናቀቅ በትኩረት መስራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡              

ዘጋቢ:- እያሱ ማቲዮስ