null Ministry is working to bring changes the Hydro power sector.

የሃይል ዘርፉ ለውጥ እንዲያመጣ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ፡፡

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ8 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም አቀርቧል፡፡

በዚህ ሪፖርት ከቀረቡ ጉዳዮች አንዱ የሃይል ዘርፉን የፋይናንስ አቅም ለማጠናከር የተጀመረው ለውጥ ነው፡፡

የሃይል ዘርፉ ከፍተኛ ዕዳ ውስጥ እንደሚገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የተገነቡት በብድር ሆኖ ከሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ ብድሮቹ እንደሚመለሱ ታሳቢ ተደርጎ ቢሆንም ይህ ባለመሆኑ የወለድ ክምችት ዕዳውን እንዳበዛ ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡

የዘርፉን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እንደአቅጣጫ የተያዘውም ከዚህ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የዘርፉን ጫና በማቃለል የሚጠበቀውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትሩ የታሪፍ ማሻሻያው፣ የሃይል ብክነትን ለመቀነስ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች፣ የአገልግሎት ጥራትና ብቃት እንዲሻሻልና የሴክተሩን አደረጃጀት እስከቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ድረስ ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎች የለውጡ አካል መሆናቸውን ክቡር ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ከታሪፍ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ  የተነሳውን ጥያቄ ሚኒስትሩ ሲመልሱም ታሪፍ ማሻሻያው አቅምን ያገናዘበ መሆኑን አመልክተው ተቋሙን ከኪሳራ በማላቀቅ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል እርምጃው እንደሚያግዝ ነው የገለፁት፡፡

ክፍያ ለሁሉ ጋር በተያያዘ የተነሳውንም ጥያቄ ሲመልሱ ዘመናዊ ክፍያ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ከክፍያ ለሁሉ ጋር ያለው ውልም ሐምሌ ወር እንደሚቋረጥ ተናግረዋል፡፡

ቆጣሪ ንባብ በየወሩ መነበብ እንዳለበት ያመኑት ሚኒስትሩ ለዚህም ሰራተኛ በመቅጠርና የቆጣሪ ንባብ ለማዘመን ዕቃ ግዥ መታዘዙንም በመጠቆም ስራው ግምትን ለመከላከል እንደሚጠቅምም አመላክተዋል፡፡ ቅድመ ክፍያ ለማስፋፋትም እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲሃ ዩሱፍ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ወደታች በማውረድ በኩል በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተሰራውን ስራ በጠንካራ ጎን ወስደው በምክር ቤቱ በኩል እንደችግር የተነሱ ጉዳዮች እንዲታረሙ አሳስበው በቀጣይ ዓመት የሚቀርበው ሪፖርት አሁን የታዩ ችግሮች መልሶ እንዳያቀርብ አሳስበዋል፡፡

ሪፖርቱ ብዙ ዘርፎችን ያካተተ በመሆኑ ከምክር ቤቱ አባላትና ከቋሚ ኮሚቴው ሰፋፊ ጥያቄዎች ተነስተው ሙሉ ቀን የፈጀ ውይይት ከሚኒስትሩና ከተጠሪ ተቋማት ሃላፊዎች ጋር ተደርጓል፡፡