null Ministry of Agriculture should focus on the delayed ongoing projects.

በግብርና ሚኒስቴር ስር በመከናወን ላይ የሚገኙ የግብርና ፕሮጀክቶች አፈፃጸም የተጓተተ በመሆኑ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ወደስራ እንዲገቡ ማድረግ እንደሚገባ የግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡      

ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከመንግስት በተመደበለት፣ ከልማት አጋሮች እና ከማህበረሰቡ በሚገኘው ገንዘብ በ4 ዋና ዋና ዘርፎች ስር በመከናወን ላይ ያሉ የ16 ሮጀክቶች አፈፃጸምን ገምግሟል፡፡

የግብርና ልማት ዕቅድና ፕላን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዜና ሀ/ወልድ የሮጀክቶችን አፈፃጸም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች  በሪፖርታቸው አካተው አቅርበዋል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የፕሮጀክቶቹን አፈፃጸም ሪፖርት ካዳመጠ በኋላ በርከት ያሉ ጥያቄዎችን ያቀረበ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው በጀት፣ ጥራትና ጊዜ ሳይፈጸሙ መጓተታቸውና ሀገሪቱን የእንስሳት ሀብት ወደ ውጪ ኤክስፖርት በማድረግ አርብቶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻልና የኮንትሮባንድ ንግድን ለማስቆም የሚያስችል 4 የእንስሳት ኳረንተይን ጣቢያና 1 ቼክ ፓለት ግንባታ በ2004 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም ከአንዱ በስተቀር ሌሎቹ ስራ አለመጀመራቸውን በተመለከተ የቀረቡት ይኙበታል፡፡

የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ሃላፊዎች በበኩላቸው ለፕሮጀክቶቹን አፈፃጸም መዘግት የተለያዩ ምክንቶች ያቀረቡ ሲሆን  የአቅም ውስንነት፣ በአገሪቱ የተከሰቱ አለመረጋጋቶች እና ቡዙዎቹ ፕሮጀክቶች ራቅ ያሉና ጠረፍ አካባቢ መገኘታቸውን በዋናነት አንስተው ፕሮጀክቶቹ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምሩ ምላሽ ተሰጥተዋል፡፡

የእንስሳት ሀብት ወደ ውጪ ኤክስፖርት በማድረግ አገሪቱ በዘርፉ ተጠቃሚ ለማደረግ ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ወደስራ ቢገባም ገንዘቡ የተገኘው በቅርቡ በመሆኑ እስካሁን የተሰሩት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሆኑ፣ ከቀጣዩ አመት ጀምሮ ግን ወደ ተጨባጭ ስራ እንደሚገባ ነው የሚ/ር መ/ቤቱ የስራ ሃላፊዎች የገለጹት፡፡          

የቋሚ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ ውስንነት ቢኖርባቸውም ወቅታዊ ሁንታዎችን በመቋቋም የተወሰኑ ፕሮጀክቶች አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ወደ ስራ መግባታቸውን፣ ወደተጨባጭ ስራ ለመግባት የሚስችሉ የአሰራር ማንዋል መዘጋጀታቸውን በጠንካራ አፈፃጸም አንስተዋል፡፡

በመጨረሻም የፕሮጀክቶችን መጓተት ለመቅረፍ ቅንጅታዊ አሰራርን በቀጣይ ማጠናከር እንደሚገባ፣ የእንስሳት ኳረንተይን ወደስራ መግባት እንዳለበት፣ አመራሩ አሁንም የአቅም ግንባታ ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እና ለፕሮጀክቶቹ ከመንግስት፣ ከልማት አጋሮች እና ከማህበረሰቡ የሚሰበሰበው ገንዘብ በትክክል በስራ ላይ መዋሉን ማረጋጥ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡