null Ministry of Innovation and Technology should focus on indigenous technological innovations for they have positive impacts on the national economy.

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ስራዎች ለአገር ኢኮኖሚ ያላቸውን አስተዋጽኦ በመረዳት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ  መስራት እንዳለበት ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው  መጋቢት 17 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌደሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 29ነኛ መደበኛ ስብሰባው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የ20011 በጀት አመት የ9 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባዳመጠበት ወቅት ነው፡፡

 ሪፖርቱን ያቀረቡት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ  ዶ/ር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ፤ ፈጠራ ፣ቴክኖሎጂና ሀገር በቀል ዕውቀቶች ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ድርሻ በተመለከተ የተለያዩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ከሚለሙ ሲስተሞች መካከል የአሰራር ስርአቶችን የሚያዘምኑ ሶፍትዌሮች ፣ የብዝሃ ህይወት መረጃ ስርአት፣የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ምዘና ሲስተም እንዲሁም ለ4 ተጨማሪ ተቋማት የአሰራር  አፕሊኬሽኖች በልጽገው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስትቲዩት የሸንኮራ አገዳ መጭመቂያ ማሽን ፕሮቶታይፕ ዲዛይን ተጠናቆ ወደ ፕሮቶታይፕ ግንባታ መገባቱን፣ ፕላስቲክና አሸዋን በመቀላቀል የወለል ንጣፍ  ፕሮቶታይፕ ማጠናቀቅ መቻሉንና በኢንስቲትዩቱ ከሚደገፉ ምርምሮች ውስጥ ባህላዊ ጠጅን በዘመናዊ መንገድ የሚያመርት የምርምር ስራን ድጋፍ ተደርጎ መጠናቀቁን እንዲሁም የቡናን ተረፈ ምርት ወደ ማዳበሪያ መቀየርና ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን  እና ሌሎችንም በርካታ ተግባራት አብራርተዋል፡፡

የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የምርምር ውጤቶችን ማሸጋገርና ጥቅም ላይ ለማዋል አስቻይ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች  በላብራቶሪዎችና በዳታ ማዕከላት ለማደራጀት የተደረገው ጥረት ጥሩ መሆኑንና ሊቀጥልና ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል፡፡

የባዮ ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ለአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተሰሩ ስራዎች፣ በምርምር ስራዎች ላይ ሴት ተመራማሪዎችን በብዛት ለማሳተፍ የሚደረገውን ጥረት በጥሩ ጎን አንስቷል፡፡

በሌላ በኩል የመንግስት ተቋማት በፍጥነት በአስተማማኝ ኦን ላይን የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የኦቶሜሽን ስራው፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ያለውን ፋይዳ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ የህዝብ ክንፎችን በማስተሳሰር የዘርፉን ተልዕኮ ለማሳካት በቀጣይ ተጠናክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አንስቷል፡፡

የምርምር ውጤቶችን  አገልግሎት ላይ ማዋል፣አገር በቀል ቴክኖሎጂዎችንና የፈጠራ ስራዎች ለአገር ኢኮኖሚ ያላቸውን አስተዋጽኦ በመረዳት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ  መሰራት እንዳለበት፣የጨረራ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም  ተደራሽነት ሽፋንን ማሳደግ ረገድ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡ በተጨማሪም የሰው ሃይል ማሟላትና ያሉትንም  ባለሞያዎች አቅም መገንባት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን አንስቶ በቀጣይ ሊስተካከል እንደሚገባ ገልጿል፡፡

ከቋሚ ኮሚቴውና ከምክርቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን  ክቡር ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም ምክር ቤቱ  በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ያለ የዋስትና መብት ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለህግ፣ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በ2 ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ መርቷል፡፡