null Ministry of Peace said that the role and support of regional states in bringing individuals and political leaders into verdict.

ግጭት በማስነሳት የተጠረጠሩ ግለሰቦችንና አመራሮችን ለህግ ለማቅረብ በተጀመሩ የምርመራ ስራዎች  የክልሎች ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን የሰላም ሚኒስቴር ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ፡፡

የሰላም ሚኒስቴር የበጀት ዓመቱን የስድስት ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም አቅርቧል፡፡

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮችን ወደመኖሪያ ቀያቸው መመለሻቻን፣ ተፈናቅለው ላሉ ዜጎችም የዕርዳታ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ፣ በግጭት የተሳተፉ ከ900 በላይ ተጠርጣሪዎችን ምርመራ አድርጎ ለህግ ማቅረቡን፣ ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

አገራዊ ፍቅርን ለማስጨበጥ የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም በሚኒስቴሩ መስሪያ ቤቱ በኩል ስለመጀመሩ ሪፖርቱ  ከማመላከቱ ባሻገር ሚ/መስሪያ ቤቱ ያልተሻገራቸው ችግሮችም ተጠቁሟል፡፡

ሪፖርቱን ተከትሎ ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን በሰላም ዙሪያ ሲያወያይ መቆየቱን አስታውሶ እነዚህ መድረኮች በሀገሪቱ መረጋጋትን ከመፍጠር አንፃር ምን ውጤት እንዳበከተ እንዲብራራ፣ በመድረኮቹ በመጠቀም ግጭት በሚነሳባቸው አካባቢዎች የግጭቶቹን መንስኤዎች ስለመለየቱ፣ ከተለዩ ምን እንደሆኑና መፍትሔስ እየተፈለገላቸው ስለመሆኑ እንዲብራራላቸው ጠይቋል፡፡ እንደዚሁም ግጭቶችን ቀድሞ ከመተንበይና ከመከላከል አንፃር ያለው ሁኔታ እንዴት እንደተገመገመም እንዲገለፅ ጠይቋል፡፡

በየአካባቢው የተፈናቀሉ ህብረተሰቦች የተሟላ ድጋፍና ዕርዳታ እንዲያገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ስላለው ሁኔታ፣ የወደሙና የተዘረፉ ንብረቶች ከማስመለስ እና ህገ ውጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መልክ ከማስያዝ አንፃርም የተሰራ ስራ እንዲብራራ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል፡፡

ሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሚና ሁኔታዎችን ማመቻቸት በመሆኑ በርካታ አካላት ሰላምን አጀንዳቸው አድርገው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ ረገድ ጅምር ውጤቶች መታየታቸው መገምገሙን፣ የነበሩ ግጭቶች ስለመቆማቸው፣ የሚመለከታቸውን አካላት ለማቀራረብ ስለመቻሉ፣ መረጋጋት ስለመፈጠሩ እና በአንዳንድ ማህበረሰቦች መካከል ዕርቀ ሰላም ስለመውረዱ በመጥቀስ ስለታየው ጅምር ውጤት አብራርተዋል፡፡ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበቱን ሁኔታ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መፍጠሩን በመግለፅ በአገሪቱ አራቱ አቅጣጫዎች ስለተሰሩ ስራዎች ማሳያዎችን አቅርበዋል፡፡

የግጭት መንስኤዎች ብዙ እንደሆነ ያመለከቱት ሚኒስትሯ የብሔር መልክ ያለው፡ ሌሎች ባህሪያት ያሉት የቆዩ መዋቅራዊ የሆኑ ችግሮች እንደሆኑ ነው የተገለፀው፡፡

አክለውም ብዙ ቦታ ግጭቶች በአመራሩ ተሳትፎ የተፈፀሙ መሆናቸውን አስረግጠው የተናገሩት ክብር ሚኒስትሯ ጥቃቶቹ ከክልሎች ስም ጋር በመያያዙ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን አሳልፎ ከመስጠት አኳያ ትብብራቸው አነስተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ የወንጀል ምርመራ ቡድኑ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡

ግጭት ቀድሞ ከመከላከል አንፃር ዘላቂ የሰላም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱና በመረጃ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ስራዎችን አስፍቶ እየተሰራ ያለው ስራ ግጭቶችን አስቀድሞ የመከላከል ስራ አካል መሆኑን ሚኒስትሯ ለማብራራት ሞክረዋል፡፡

የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም አንድ ሚሊዮን ያህል ዜጎች ወደቀያቸው መመለሳቸውን ጠቁመው ቁጥሩ ግን ከመፈናቀሉ ጥቅም የሚያገኙ አካላት አጋነው ስለሚገልፁ የማጣራት ስራ ተሰርቶ ሪፖርት እንደሚቀርብ ለኮሚቴው ቃል ገብተዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት መልሶ ግንባታ ግን ችግሩ ከበድ ያለ መሆኑን በመግለፅ ከመንግስት ባሻገር የህብረተሰቡና የረጂ አካላት ተሳትፎን እንደሚጠይቅም ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በርካታ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን አቅርበው በሚኒስትሯ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በውይይቱ ማጠቃለያ የኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ በሰጡት አስተያየት የተሸረሸሩ የሰላም እሴቶች ተመልሰው እንዲገነቡ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ስለተሰሩ ስራዎች፣ ብሔራዊ የሰላም መዝሙር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለበላይ አካላት ስለመቅረቡ፣ የዘላቂ ሰላም ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ እንደሚመለከት ጠቁመው፤ ተጠርጣሪዎችን ለህግ የማቅረቡን ስራ ግን ሚንስቴር መ/ቤቱ ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንዳለበት ነው ያሳሰቡት፡፡