null Recorded Information of clean water supply is not fairly managed.

የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መረጃ በአግባቡ እየተያዘ ያለመሆኑ ተጠቆመ

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ8 ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረበበት ወቅት በተደረገው ውይይት የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አቅርቦት መረጃ አያያዝ ላይ ክፍተት መኖሩን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አመለከቱ፡፡

በቀረበው ሪፖርት ሚኒስትሩ በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ሀገራዊ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋንን ከ71.1 በመቶ ወደ 77 በመቶ ለማድረስ ግብ ተጥሎ በዋና ዋና ፕሮጀክቶች ላይና በውሃ ፈንድ በኩል በተሰሩ ስራዎች በ8 ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ ሽፋኑን ወደ 72.7 ማድረስ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

የአቅርቦቱ ሽፋን ትክክል ስለመሆኑ ከምክር ቤቱ ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ የተቋሙ መረጃ አያያዝ ባህላዊ በመሆኑ ችግሮች እንዳሉት ጠቁመው ይህን ለማስተካከል 3924 ታብሌቶች ተሰራጭተውና ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጥቶ ቆጠራው በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የጠራ መረጃ የሚቀርብበት ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ በፊት ለነበረው ክፍተት ምክር ቤቱን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ በ8 ወራት ለመጣው 1.6 በመቶ አገራዊ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ጭማሪ ስላልተሰሩ ስራዎች ዝርዝር ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ አንድ ዋሽ ፕሮግራም በአገር አቀፍ ደረጃ በ382 ወረዳዎችና በ144 ከተሞች ላይ ንፁህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ለማቅረብ በተሰራው ስራ በከተሞች 375326 እና በገጠር 3692094 ነዋሪዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከአምስት ትላልቅና መካከለኛ ከተሞች የመጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክት የመቀሌና የሀዋሳ ከተሞች ፕሮክቶች ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቃቸው ባጠቃላይ 560298 ነዋሪዎችን የንፁህ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ሪፖርቱ ጠቅሟል፡፡ የቦንጋና የደምቢ ዶሎ ከተሞች ፕሮጀክቶችም ተጠናቀው 70000 ነዋሪዎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎችን ለመታደግና አስቸኳይ የውሃ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን ለማዳረስ እየተሰሩ ስላሉ ስራዎችን ሪፖርቱ አካቶ ይዟል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን በተለያዩ የስራ ሃላፊዎች በቂ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ፈቲሃ ዩሱፍ በከፍተኛ ወጪ የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች መምከንና ለጤና ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች እየተገኙባቸው የውሃ ጉድጓዶቹ መታሸግ የሀብት ብክነት መሆኑን አመልክተው ችግሮቹን ለመቀነስ አስቀድሞ ጥናቶች እንዲደረጉ አሳስበዋል፡፡