null Repeated plane crash an obstacle to the protection of desert locusts.

ተደጋጋሚ  የአውሮፕላን ብልሽት የበረሃ አንበጣን ለመከላከል እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ

ጥቅምት 26 ፣ 2012 ዓ.ም ፤ ተደጋጋሚ  የመርጫ አውሮፕላን ብልሽት የእድገት ደረጃውን ጨርሶ እንቁላል ለመጣል በሚያስችለው ደረጃ በሰኔ ወር አጋማሽ  2011 ዓ.ም ወደ ሃገራችን የገባውን  የበረሃ አንበጣ  ለመከላከል  እንቅፋት እንደሆነበት የግብርና ሚኒስቴር  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  አስታወቀ፡፡

ይህ የተገለጸው የግብርና ፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ቋሚ የሚኒስቴሩን የ 2012 ዓ.ም በጀት አመት የአንደኛ ሩብ አመት እቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

በትግራይ ክልል ሰባት ወረዳዎች ፣ በአማራ ክልል አስር ወረዳዎች ፣ በኦሮሚያ ክልል ዘጠኝ ወረዳዎች ፣  በሶማሌ ክልል አስራ ሁለት ወረዳዎች ፣ በአፋር ክልል ሃያ አንድ ወረዳዎችና በድሬዳዋ መስተዳደር አንድ ወረዳ  ላይ  ከሰኔ 2011 ዓ.ም  እስከ ጥቅምት 2012 ድርስ የበረሃ አንበጣው ያረፈባቸው ሲሆኑ የመከላከል ስራው ተጠናክሮ እንደቀጠለም በግብርና በሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ስላቶ ተናግረዋል፡፡

የመከላከል ስራውን ፈታኝ ካደረጉት መካከል አንበጣው ያረፈባቸው አካባቢዎች በአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ አመች አለመሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከጎረቤት ሃገሮች ያልተቋረጠ የአንበጣ መንጋ ወደ ሁሉም ክልሎች መዛመት ፣ የአየር ጸባዩ ለአንበጣው  መራባት ምቹ መሆኑ ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የወረዳና ቀበሌ አመራሮች ለችግሩ ትኩረት ማነስ ለመከላከል ስራው እያጋጠሙ ካሉት  ችግሮች መካከል  መሆናቸውን  አቶ ዘብዲዎስ ጠቅሰዋል፡፡

በአፋርና ሶማሌ ክልሎች በአውሮፕላን ፣ መኪናና በሰው ሃይል በመታገዝ 95 በመቶ የበረሃ አንበጣውን መከላከል እንደተቻለም አቶ ዘብዲዎስ አክለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከፍተኛ የመሬት ሽፋን ያለው አዳጊ አንበጣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች እንደተፈለፈለና አንበጣው ባረፈባቸው ቦታዎች ህዝብ የሰፈረ አለመሆኑን ችግሩን እንዳባበሰው አቶ ዘብዲዎስ  ጠቅሰዋል፡፡

 የበረሃ አንበጣውን በሙሉ አቅም ለመከላከል  ከፌደራል 20 እንዲሁም ከክልሎች 17 መኪና መሰማራቱን የግብርና ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ ሳኒ ረዲ ገልጸዋል፡፡

ከፌደራል 26 እንዲሁም ከክልሎች 226 ባለሙያዎች ለዚሁ ስራ መሰማራታቸውንም አቶ ሳኒ ተናግረዋል፡፡

«ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚደርስልን የበረሃ አንበጣው ጉዳት ካደረስብን በኋላ ነው እያለ የመረጠን  ህዝብ ይነግረናል ፤ መሬት ላይ ያለውና እናንተ የምታቀርቡት ሪፖርት  አይገናኛኝም  » ሲሉ  አንድ የቋሚ ኮሚቴው አባል ተናግረዋል፡፡

የበረሃ አንበጣው ያደረሰውን የጉዳት መጠንና እየተሰራ ያለውን የመከላከል ስራ ለመመልከት ከቋሚ ኮሚቴው የተውጣጣ ሁለት ቡድን ከአርብ 28/2/2012 ጀምሮ በአማራ ፣ ትግራይ ፣ አፋር ፣ ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ መስተዳድርና ፣ ምዕራብ ሃረርጌ ዞን ላይ የመስክ ምልከታ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ነጋልኝ ዮሴፍ ገልጸዋል፡፡

አፈር ምርታማነትን ለመጠበቅ የተሰሩ ስራዎችና የስጋ ምርትን ለማሳደግ የተከናወኑ ስራዎችን ቋሚ ኮሚቴው በጥንካሬ ከጠቀሳቸው መካከል ይገኙበታል፡፡

በሌላ በኩል የእቅድና ሪፖረት አለመናበብ እንዲሁም በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ የግል ባለሃብቶችን ከመደገፍ አኳያ ትኩረት ያሻቸዋል ከተባሉት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡