null Representatives obtain clarifications from Premier on contemporary issues

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ  በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጡ

ፓርላማ ሰኔ 1 2012 ..   የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር  ዐብይ  አሕመድ  ወቅታዊ ጉዳዮችን  አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

ኮሮና ቫይረስ በአለም  ብሎም በሃገራችን  ስርጭቱ በከፍተኛ  ቁጥር  እየጨመረ መጥቷል በተለይም  በድንበር አካባቢ ያለው ቁጥጥር አነስተኛ በመሆኑ በአካባቢው  የሚገኙ ዜጎች ለከፍተኛ ስጋት እየተዳረጉ የሚገኙ ስለሆነ    በአካባቢ ያለውን የቫይረስ ስርጭት ለመከላከል  እንዲሁም  ቫይረሱ የምጣኔ ሃብቱን በተለይም  የግብርናውን  ዘርፍ እንዳይጎዳው በመንግስት በኩል ምን እየተሰራ ነው ? “  የሚሉ  ጥያቄዎች  ከምክር ቤት አባላት ቀርበውላቸዋል ፡፡

ቫይረሱ ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮች ጨምሮ  በመላ ሃገሪቷ  በከፍተኛ መጠን እንደተሰራጨ   ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ተናግረዋል ፡፡

እንደ ሃገር ቫይረሱን መከላከል ሳይሆን ያለበትንና የሌለበትን ሰው መለየት የሚያስችል ብቃት እንዳልነበረ ገልጸው ባለፉት ሶስት ወራት በተሰራው ውጤታማ ስራ በአሁኑ ጊዜ በቀን 8 ሺህ ሰው መመርመር  የሚያስችሉ 31 ላብራቶሪዎች እንዳሉ  ዶክተር ዐብይ አብራርተዋል ፡፡

በመጭው ሃምሌ ወር ላይ የላብራቶሪ ቁጥሮቹን  ወደ 38 በማሳደግ በቀን እስከ 14 ሺህ ሰው መመርምር እንደሚቻል ነው ጠቅላይ  ሚኒስትሩ የገለጹት ፡፡

ከደቡብ አፍሪካ ጋናና ሞሮኮ በመቀጠል ኢትዮጵያ 143 ሺህ ሰው የመረመረች ሲሆን ሃገሪቷ የመመርመር አቅሟችን  አጠናክራ እንደምትቀጥል  ዶክተር ዐብይ ጠቅሰዋል ፡፡

ቫይረሱን ከመከላከል ጎን ለጎን የጤና ስርዓቱን ለማዘመን 5 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተራ እንደሆነ ተገልጾ 54 የሕክምና መስጫዎች ማዕከላት   30 ሺህ የቫይረሱ ምልክት ያለባቸውን ሰዎች  እንዲሁም 17ሺህ 500  በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ማስተናገድ የሚያስችሉ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል ፡፡

በድንበርም ሆነ  በመሃል ሃገር ያለውን የቫይረሱን ስርጭት  ለመከለከልና የላብራቶሪ አቅምን ለማጠንከር   ለሁሉም ክልሎች በፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀመር አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት  የገንዘብና የአይነት ድጋፍ  መደረጉንም ተናግረው፣  ኮሮናን በተመለከተ  ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ እየቀረበ እንደሚገኝ ዶክተር ዐብይ ጠቅሰዋል ፡፡

ኮሮና በምጣኔ ሃብቱ ላይ የሚያሳርፈውን ጫና በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ማብራሪያ ሰጥተዋል ፡፡

በአለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት / International monetary fund/ ትንበያን ዋቢ በማድረግ በኮሮና ምክንያት ከ 170 ሃገራት በላይ እድገታቸው ኔጌቲቭ እንደሚሆን ዶክተር ዐብይ ገልጸዋል፡፡

  በዚህ አመት የኢትዮጵያን ምጣኔ ሃብት 9 በመቶ ለማሳደግ የታቀደ ቢሆንም በኮሮና ምክንያት 6 በመቶ እድገት እንደሚመዘገብ ተናግረዋል ፡፡

የንግድ ስርዓታችን ከአለም ንግድ ጋር ከ 30 በመቶ በታች የተሳሰረ መሆኑ ፣ የፋይናንሻል ሴክተሩ በከፍተኛ እድገት ላይ መገኘቱ  በተለይም የተበላሸው ብድር መቀነሱንና በዚህ አመት የኤክስፖርት  አቅማችን 13 በመቶ  በማደጉ እድገቱ ሊመዘገብ እንደሚችል  ምክንያት እንደሆኑ  ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል ፡፡