null Researches are not problem solving and adding values to the agricultural sector.

ምርምሮች ችግር ፈቺ በሆነ መልኩ ጥቅም ላይ ውለው ለግብርናው ዘርፍ እሴት እየጨመሩ እንዳልሆነ ተገለፀ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግብርና፣ አርብቶ አደርና አካባቢ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የ2011 ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

ኢንስቲትዩት በበጀት ዓመቱ በመስኖና መኸር የሰብል፣ የእንስሳትና በተፈጥሮ ሀብት ላይ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ብሎም በመፍጠር አሁን የተደረሰበትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረጉን ስራ አቅዶ እየሰራ መሆኑን በኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የሆኑ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ ባቀረቡት ሪፖርት አብራርተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 18 የሚሆኑ የምርምር ማዕከላት ያሉት ሲሆን በማዕከሉ ቴክኖሎጂን በማፍለቅ አርሶ አደሩ ዘመናዊ ግብርና ምርት ሂደት ውስጥ እንዲገባም የሚያችል ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በበጀት ዓመቱ በሰብል ዘርፍ 61 ቴክኖሎጂዎችን በምርምር ማፍለቃቸውንም ለአብነት ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከታቀዱት የምርምር ተግባራት 42ቱ ያልተጀጀመሩና ከተጀመሩትም 25ቱ የተቋረጡ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ቢገልጽም ኢንስቲትዩቱ በበኩሉ ሰብል ምርምር ጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም በእንስሳት ምርምር ግን ገና ያልተጀመሩ እንዳሉ እነዚህም በበጀት እጥረት፣ በግብዓት አቅርቦት ማጣትና በአካባቢዎቹ በተፈጠሩት የጸጥታ ችግር እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በምርምር የፈለቁ ዝርያዎችም ሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ተደራሽ በማድረጉ ረገድ ከፍተኛ ክፍተት እንዲኖር ያረገው ኢንስቲትዩቱን የማሳወቁ ስራ ደካማ በመሆኑ፣ አርሶ አደሩ አዲስ የመጣውን ከመጠቀም ይልቅ የነበረውን ይዞ ለመቀጠል የሚፈልግ በመሆኑ እና አቅራቢዎች ለትርፍ ብቻ የሚሰሩ በመሆናቸው አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በብዙ ጥረት ፈልቀው አገልግሎት ሳይሰጡ እንደቀሩ ገምግሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በኢንስቲትዩቱ የለሙ የቴክኖሎጂ ምርቶች ውጤታቸው ምን ያህል እንደሆነ እና በበሽታ ሳይጠቁ ለተጠቃሚው ከማድረሱም አኳያ አልፎ አልፎ ዝቅተኛ እንደሆነም ጭምር ጠቁሟል፡፡

ቋሚ ኮሚቴውም ኢንስቲትዩቱ ለአገራችን ግብርና አስጊና ማነቆ እየሆኑ የመጡ መጤ ፈጣን መፍትሔ የሚሹ ተባይና አረሞች እንደ  የአሜሪካን ተምች፣ የቡና ግንድ አድርቅ፣ የቡና ቅጠል አለብላቢ እና የውሃ አካላትን እየወረረ ያለውን እንቦጭ አረም ለመከላከል እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ለማምረት የተለያዩ ምርምሮችን በማጠናቀቅና በሽታውን ለማከም ከተለያዩ አፍሪካ አገራት ጋር እየሰሩ መሆናቸው የተብራራ ሲሆን ለቀጣይ ግን ሌሎች በኢንቨስትመንትና መሰል በሆኑ መንገዶች እንዳይገቡ ለማድረግ የሚመለከተው አካል ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ መወጣት እንዳለበት ነው የተነሳው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኢንስቲትዩቱ አንዳንድ አካባቢዎች ካሉት የማህበረሰብ ጋር ያለው ግንኙነት የላላ በመሆኑ አሁን ላይ ካሉት የምርምር ማዕከላት ሁለቱን መነጠቃቸውንና ከቀሩትም አንዳንዶቹ የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው በመሆናቸው ለቀጣይ የምርምር ማዕከላትን ህልውና በማመናመን አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንዳይጥል በማብራሪያው ተነስቷል፡፡

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ኢንስቲትዩቱ አገሪቱ ከግብርናው መር ወደ ኢንዱስትሪው ለመሸጋር በምታደርገው ጥረት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከምንም በላይ ድርሻው የጎላ ቢሆንም ዘርፉ መጠቀምና ማምጣት ባለበት ልክ ለውጥ ለማምጣት ብሎም የቴክኖሎጂውን ሽግግርን ለማስፋት በርካታ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ መጣር እንዳበትም አሳስቧል፡፡