null Speaker of the House of Peoples' Representatives, Tagesse Chaffo, said that he is working to increase public participation in the country's legislative process.

በአገሪቱ የህግ አወጣጥ ሂደት ውስጥ የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግ እየተሳራ እንደሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ፣

አፈ-ጉባኤው የጀርመን ፓርላማ ልዑካን ቡድንን  በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡

የውይይቱ ዓላማም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የፓርላማ ዲፕሎማሲ እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማሳደግ እንደሆነም ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአዲስ የለውጥ ሂደት ላይ እንደምትገኝና ለውጡም በጥሩ ሁኔታ ወደፊት እየተጓዘ እንደሆነ የተነገሩት አፈ-ጉባኤው ለዚህም ለውጥ አላሰራ ያሉ ህጎችን ከማሻሻል ጀምሮ ተገቢ ውሳኔዎችን በመወሰን ረገድ የፓርላማው አስተዋጽኦም ከፍተኛ ነበር ብለዋል፡፡

በአገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ከማስፋት አኳያ የታሰሩ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎችና ጋዜጠኞችን የማስፈታት እና በአሸባሪነት ተፈርጀው ከአገር የተሰደዱ አካላት ወደ አገራቸው እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች በትኩረት የተሰሩ ሲሆን ይህም አገሪቱ በለውጥ ሂደት ውስጥ የመሆኗ ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

የህግ አወጣጥ ሂደቱን የተሳካ ከማድረግ አኳያ ፓርላማው ዜጎችን በቀጥታ ተሳትፎና በነፃ የስልክ መስመር እያሳተፈ መሆኑን ያነሱት አፈ-ጉባኤው ይህንኑ ከማስፋትና የህዝብ ተደራሽነትን ከማሳደግ አንፃር አሰራሩን ማዘመን እንደሚያሰፈልግም ተናግረዋል፡፡

የጀርመን ፓርላማ ልዑካን ቡድን አባለት በበኩላቸው ሁለቱ አገራት የቆዬ የወዳጅነት ታሪክ ያላቸው እንደሆኑ አንስተው የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ስዓት እያካሄደ ያለውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁና የጀርመን መንግስት ለለውጡ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር አጠናክራ እንደምትቀጥል የገለጹት የቡድኑ አባላት የሁለቱን አገራት የፓርላማ ዲፕሎማሲና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር አኳያ አስፈላጊውን የቴክኖሎጅ ድጋፍ እንደሚያደርጉና በተለይም የፓርላማውን ላይበራሪ ለማዘመን የሚያስችል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡