null Speaker Tagesse Chafo said legal measures will be taken against leaders who did not take actions for their audit findings.

የኦዲት ግኝቶችን ያላስተካከሉ ሃላፊዎች ለህግ እንደሚቀርቡ አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ፡፡ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የቅጣት ህጎች አሁን ወደተግባር እንደሚሸጋገሩ አሳሰቡ፡፡

ከ2002 እስከ 2008 በጀት ድረስ የተሰጡ የኦዲት አስተያየቶችን ያላስተካከሉ የመንግስት ሃላፊዎች ከአዲሱ በጀት ዓመት በፊት የማስተካከያ እርምጃዎችን  እንዲወስዱ የሚያሳስብ የምክክር መድረክ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ተካሄደ፡፡

የምክክር መድረኩን የመሩት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ የውይይቱ ዓላማ የኦዲት ግኝቶቹን ያላስተካከሉ የመንግስት ሃላፊዎችን ለህግ በቀጥታ ከማቅረብ በፊት ወደእርምት እርምጃ እንዲገቡ ለማሳሰብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለመንግስት እንዲመለስ የኦዲት አስተያየት የቀረበበት የገንዘብ መጠን ብር 2.1 ቢሊዮን መሆኑን አስታውሰው ገንዘቡን ለማስመለስ ባለው የቁርጠኝነት ማነስ እስከ አሁን ድረስ የተመለሰው ገንዘብ 50 ሚሊዮን አካባቢ ብቻ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡ እንዲመለስ የተጠየቀው ገንዘብ ህግና መመሪያ ባለማክበር የወጡ፣ መክፈል ከሚገባ በላይ የተከፈሉ፣ የውል ህግ ሲጣስ ቅጣቶችን ካለማስከፈል የቀሩ፣ ታክስ ሳይቆረጥ የተፈፀሙ ክፍያዎች፣ ቅድመ ክፍያ ሳይመለስ የቀረ፣ የጥሬ ገንዝብ ጉድለት የመሳሰሉ እንደሆኑ በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡

የኦዲት ግኝቶችን የማያስተካክል ሃላፊ ከ10 ሺ እስከ 30 ሺ በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ የዋና ኦዲተር ማቋቋሚያ አዋጅ የሚደነግግ ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ ያለመደረጉን ጠቁመው አሁን ግን ህጉ ወደመሬት የሚወርድበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው ያሳሰቡት፡፡

ጠቅላይ አቃቤ ህግ በበኩሉ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ 15 የፌዴራል መንግስት ተቋማትን በብር 408 ሚሊዮን እና 20 ዩኒቨርሲቲዎችን በብር 692 ሚሊዮን ለይቶ ለምርመራ ስራ የሚያግዝ ጭብጥ መለየቱን፣ የምርመራ መዝግብ ማደራጀቱንና ለተቋማት የሚላኩ ደብዳቤዎች መዘጋጀታቸውን ነው ያብራራው፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ ባለበጀት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች የተሰጠው ጊዜ በቂ ያለመሆኑንና በተለይም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉባቸው ተጨባጭ ችግሮች እንዲታይላቸው አስተያየቶችን  አቅርበዋል፡፡

የተከበሩ አፈ ጉባኤውና ዋና ኦዲቱ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርቦ በተጨባጭ ስራ ውስጥ ተገብቶ የሚታዩ ችግሮች መፍትሔ ከሚፈለግላቸው ውጭ የኦዲት ግኝቶቹ ተፈፃሚ ሳይሆኑ ከቆዩበት ጊዜ በላይ ሌላ ተጨማሪ ጊዜ እንደማያስፈልግ ነው ያሳሰቡት፡፡

 ፀረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽንም የኦዲት ግኝቱን ለመተግበር መስሪያ ቤቶች የሚያቅማሙት ምክር ቤቱ እርምጃ የማይወስድ መሆኑን በማመልከት የኦዲት ግኝቱ ላይ ድርድር እንደማያስፈልግ የራሱን አቋም አራምዷል፡፡

 ተሰብሳቢዎችም የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ከመጋቢት 17 ቀን ጀምሮ ወደትግበራ እንደሚገቡ ስምምነት ተደርሶ የውይይቱ ፍፃሜ ሆኗል፡፡